በንጹሃን ላይ ጉዳት የደረሰው በቦንብ፣በሚሳየል እና በአየር ጥቃት መሆኑን ተመድ ገልጿል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ዛሬ ባወጣው መግለጫ 14ኛ ቀኑን ባስቆጠረው የዩክሬን ጦርነት 416 ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል፡፡
የተመድ የሰብአዊ መብት ቢሮ እንደገለጸው ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ 1424 ንጹሃን ሰዎች በሁለት ሳምንት ውስጥ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል 516 የተገደሉ ሲሆን 908 የሚሆኑት ደግሞ መቁሳላቸውን ማረጋገጡን ተመድ ገልጿል፡፡
ተመድ ቁጥሩ ከዚህ በላይ ሊሻቅብ ይችላል ብሏል፡፡
በንጹሃን ላይ ጉዳት የደረሰው በቦንብ፣በሚሳየል እና በአየር ጥቃት መሆኑን የገለጸው ተመድ በቫልኖቫካ፣በማሪፖል እና እዚውም ግዛት ያለው ጥቃት መጠን እየተጠና ነው ብሏል፡፡
በምእራባውያን የምትደገፈው ዩክሬን፣ ምእራባውያን በዩክሬን ከበረራ ነጻ ቀጣና እንዲያውጁ ብትጠይቅም፤ ምእራባውያን ርምጃው ቢወሰድ ከሩሲያ ጋር በቀጥታ ስለሚያጋጭ አናውጅም ብለዋል፡፡
የምእራባውያን ወታደራዊ ጥምረት በሆነው የኔቶ ድክመት ሰዎች ህይወታቸውን ያጣሉ ሲሉ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በትናንትናው እለት ተናግረዋል፡፡
ምእራባውያን ይህን ባለማድረጋቸው ዩክሬን ብቻዋን እየዋጋች ነው ሲሉ ዘለንስኪ ተደምጠዋል፡፡
ቭላድሚር ፑቲን ደግሞ “በዩክሬን የተጀመረው ወታደራዊ ተልዕኮ” ሀገራቸው ባቀደችው መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሩሲያ ጦር እስካሁን ባካሄደው “ዘመቻ” በደቡብ ዩክሬን የምትገኝው ኬርሶን ከተማ ጨምሮ ሌሎች ቦታዎችንና ከተሞችን መቆጣጠር ችሏል፡፡ የሩሲያ ወታራዊ ዘመቻ በምዕራባውያን ዘንድ ያልተወደደ በመሆኑ በርካታ የኢኮኖሚ ማዕቀቦች ጎርፍ እየወረደባት ነው፡፡ ምዕራባውያን የኢኮኖሚ ማእቀብ ከመጣል በተጨማሪ የአየር ክልላቸውን ለሩሲያ ዝግ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ ባደረገው ስብሰባ ሩሲያ ዩክሬንን መዉረሯን የሚያወግዘዉን የዉሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት የከፈተችው፣የኔቶ ጦር ዩክሬንን ጨምሮ ወደ ቀድሞ የሶቬት ህብረት ሀገራት እተሰፋፋ ነው፤ይህም ለደህንነቷ አስጊ እንደሚሆን በመግለጽ ነበር።የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት እደቀጠለ ቢሆንም ሀገራቱ ችግሩን ለመፍታት ውይይታቸውን ጀምረዋል።