በትግራይ ኤርትራውያን ስደተኞች መገደላቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች ደርሰውኛል- የተመድ ስደተኞች አጀንሲ
የሪፖርቶቹን ትክክለኛነት ለመገምገም የሚረዱ ተገቢ መረጃዎችን እየሰበሰበ እንደሆነም ተመድ አስታውቀዋል
መከላከያ ከትግራይ መውጣቱን ተከትሎ በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ግድያ እየተፈጸመ እንደሆነ ሪፖርቶች እየወጡ ነው
በትግራይ ክልል ሽሬ አካባቢ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች መገደላቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች ደርሰውኛል ሲል የተመድ ስደተኞች አጀንሲ ገለጸ::
በኢትዮጵያ የተመድ ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ቃል አቀባይ ኔቨን ክሬቨንኮቪክ ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት ከኦንላይን እና ከሌሎች ምንጮች በትግራይ ክልል ሽሬ ኤርትራውያን ስደተኞች መገደላቸውን የሚገልፅ ሪፖርት ባለፈው ሳምንት እንደደረሳቸው አስታውቋል።
ቃል አቀባዩ ለአል ዐይን አማርኛ በላኩት ኢሜኤል፥ " የደረሱንን ሪፖርቶች በልዩ ትኩረት ነው የምንመለከተው፤ ወዲያውኑ ሽረ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞችን ፣ ባልደረቦቻችንና ሰራተኞቻችን አግኝተናል" ብሏል።
ቃል አቀባዩ ኔቨን ክሬቨንኮቪክ “እስካሁን የደረሱን ማናቸውም ክሶች ማረጋገጥ አልቻልንም ነገር ግን የእነዚህን ዘገባዎች ትክክለኛነት ለመገምገም የሚረዱ ተገቢ መረጃዎችን መሰብሰባችንን እንቀጥላለን” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት የሀገር መከላከያ ከትግራይ ወጥቻለው ማለቱን ተከትሎ በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ግድያ እየተፈጸመ እንደሆነ የተለያዩ ሪፖርቶች እየወጡ ይገኛሉ፡፡
በትግራይ ግጭት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ስደተኞች ያሉበት እንደማይታወቅ በኢትዮጵያ የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩ ኤን ኤች ሲአር) ቃል አቀባይ የነበሩት ኤሊዛቤት አርንስዶርፍ ከአንድ ወር በፊት ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነራቸው ቆይታ ገልጸው ነበር፡፡
ቃል አቀባይዋ ሕፃፅና ሽመልባ የተባሉት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች መውደማቸውንና ስደተኞቹ የሰብአዊ እርዳታ የማግኘት ችግር እንደገጠማቸው በወቅቱ ተናግረው ነበር፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ከ8 ወር በኋላ የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ የህወሓት ኃይሎች ለውጡን በመደገፍ አብረውኝ ሲሰሩ በነበሩ ዜጎች ላይ ጥቃትና ግድያ እየፈጸሙ ነው ሲል ይከሳል፡፡መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ያወጀው እና ወታደሮችን ከመቀሌ ያስወጣው በፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑንም መግለጹ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል ወጣቱን ካስታወቀ በኋላ የትግራይ ኃይሎች የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌን ጨምሮ ሌሎች አካባዎች መቆጣጠር ችለዋል፡፡
የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ሮዝመሪ ዲካርሎ መንግስት ያስተላላፈው የተከስ አቁም ውሳኔ ህወሓትን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች ሊጠቀሙበት የሚገባ እድል ነው፤ የህወሓት ኃይሎችም ተኩስ አቁሙን “በአስቸኳይና ሙሉ በሙሉ” ሊደግፉት ይገባል ሲሉ በትግራይ ቀውስ ጉዳይ ለተሰበሰበው የጸጥታው ም/ቤት መናገራቸው ይታወሳል፡፡