“ዘመቻው ህወሓትን የማጥፋት እንጂ መሬት የማስመለስ ብቻ አይደለም”- አቶ ግዛቸው ሙሉነህ
ህወሓት በክልሉ “የፈጸመውን ጥቃት” ተከትሎ ለተፈናቀሉ ከ485 ሺ በላይ ዜጎች ድጋፍ ማድረግ መጀመሩንም ነው የገለጹት
ክልሉ በዘመቻው ቦታ የማስለለቅ ብቻ ዕቅድ እንደሌለውም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል
የአማራ ክልል መንግስት ህወሃት አሁን ከያዛቸው ቦታዎች የማስለቀቅ ብቻ ሳይሆን ቡድኑን ሙሉ ለሙሉ የማጥፋት ዘመቻ ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ “ህወሓት እያለ ኢትዮጵያ ሰላም አታገኝም” ብለዋል፡፡
በመሆኑም ዘመቻው “ቡድኑን እስከመጨረሻው የማጥፋት” እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡
አሁን ላይ በግዳጅ ላይ የሚገኙ የጸጥታ ኃይሎች እየወሰዱት ባለው እርምጃ ህወሓት ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ኪሳራ እንዳጋጠመውም ዋና ዳይሬክተሩ ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
ህወሓት በሚሄድበት እና በሚደርስበት ቦታ ሁሉ የመደምሰስ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ያነሱት አቶ ግዛቸው ውጊያው ወደተሟላ ማጥቃት መሸጋገሩንም ጠቁመዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ “የውጭ ጠላቶች” በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለህወሓት ድጋፍ ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡ ሆኖም “የውጭ ጠላቶች” ያሏቸው እነማን እንደሆኑ በዝርዝር አልገለጹም፡፡
አቶ ግዛቸው የፌዴራል መንግስት የሕግ ማስከበር ዘመቻ ካወጀበት ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከአማራ ክልል በድምሩ ከ485 ሺ በላይ ዜጎች ተፈናቀለዋል ያሉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ300 ሺ በላይ የሚሆኑት በቅርቡ ህወሓት በአማራ እና በአፋር ክልሎች ጥቃት ከፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ የመኖሪያ ቀያቸውን የለቀቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ተፈናቃዮቹን ለመደገፍ የሚያስችል ስራ በመንግስት እና በለጋሽ ተቋማት መጀመሩንም ነው አቶ ግዛቸው የተናገሩት፡፡
ህወሓት በአማራ ክልል “ዜጎችን ከመግደል ጀምሮ መንደሮችን እስከማውደም እና ንብረቶችን እስከመዝረፍ የደረሱ ወንጀሎች” መፈጸሙንም ገልጸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ከቀናት በፊት ህወሓት በክልሉ የሠሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ዋና ከተማ በሆነችው ወልድያ ከባድ መሳሪዎችን በመተኮስ በንጹኃን እንዲሁም በሼክ ሁሴን መሐመድ አሊ አል አሞዲ ስታዲዬም እና በሕዝብ መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን ለአል ዐይን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ከሰሞኑ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ደብረታቦር ከተማ ተመሳሳይ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ተፈጽሞ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ 5 ሰዎች እና አንድ ተከራይ መገደላቸውም አይዘነጋም፡፡
“ህወሓት በተለያዩ ግንባሮች ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ እያጠቃን ነው” ያሉት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር የክተት ጥሪ ማስተላለፋቸው የሚታወስ ነው፡፡