በተደረገው ውጊያ ከሞቱት በተጨማሪ ከ4 ሺህ በላይ ተዋጊዎች ቁስለኛ እና ምርኮኞች ናቸውም ተብሏል
“5 ሺህ 600 የህወሓት ታጣቂ ሀይል ደምስሻለሁ” አለ የመከላከያ ሰራዊት በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ።
የመከላከያ ሚኒስቴር የሠራዊት ግንባታ ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ ዛሬ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባርተኝነት የተፈረጀው የህውሓት ቡድን ከ101 እሰከ 103ኛ ባሉ ኮሮች ውስጥ ያሉት ክፍለ ጦሮች ሙሉ በሙሉ መደምሰሳቸውን ሌተናል ጀነራል ባጫ ተናግረዋል።
መከላከያ ሰራዊት፤የክልል ልዩ ሀይሎች እና ሚሊሻዎች በህወሀት ተዋጊዎች ላይ በሰነዘሩት ጥቃት ከ5600 በላይ የህወሀት ተዋጊዎች ሲደመሰሱ፤ ከ2 ሺህ 300 በላይ ቆስለዋል እንዲሁም 2000 የሚሆኑት ተማርከዋል ብለዋል።
በዚህም የህወሓት ሃይል በሶስት አቅጣጫ ያሰለፈው ቡድን ሙሉ በሙሉ መደምሰሱንም ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ ተናግረዋል።እንደ መግለጫው ከሆነ በጀነራል ምግበይ የሚመራው አርሚ አንድ ተብሎ የሚጠራው ሃይል ሙሉ ለሙሉ ተደምስሷል ብለዋል።
“በጀነራል ምግበይ የሚመራው እና አርሚ አንድ የሚባለው ሃይል በሁመራ አካባቢ ደባርቅ እና ዳባትን በመቁረጥ ጎንደርን ለመያዝ ቢፈልግም ሙሉ ለሙሉ ተደምስሷል” ብለዋል ሌተናል ጀነራል ባጫ።
አርሚ ሁለት የሚባለው እና በሜጀር ጀነራል ዮሐንስ ወ/ጊዮርጊስ የሚመራው ሃይል በጋሸና ከክምር ድንጋይ ጀምሮ በተደረገ ውጊያ ሁለቱ ክፍለ ጦሮች እንደተደመሰሱም ተገልጿል፡፡
አርሚ ሦስት የሚባለው እና በብርጋዴር ጀነራል ፍስሃ የሚመራው በሽንፋ በኩል ከቅማንት ቡድን ጋር በመተባባር ጥቃት ቢሰነዝርም ተደምስሷል ብለዋል።
የህወሓት ታጠቂ ሀይል በተለይ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ስራ ለማስተጓጎል አስቦ ጥቃት ከፍቶ እንደነበረ የተናገሩት ሌተናል ጀነራል ባጫ፤ እቅዱ በመከላከያ ሰራዊት ተመክቷል ብለዋል።
በፌደራል መንግስትና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሃት መካከል ጥቅምት ወር 2013ዓ.ም የተጀመረው ግጭት 11 ወራትን አስቆጥሯል።
የፌደራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፤ መከላከያ ሰራዊትን ከትግራይ ክልል ካስወጣ በኋላ የህወሃት ኃይሎች የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌን ጨምሮ ሙሉ ትግራይ መቆጣጠር ቻሉ።
የህወሃት ሃይሎች ከትግራይ አልፈው በአማራና አፋር ክልል ጥቃት በመክፈት የተወሰኑ ቦታዎችን መቆጣጠራቸው ይታወቃል። አሁን ላይ ጦርነቱ እየካሄደ ያለው በአማራ አፋር ክልል ውስጥ ሆኗል።
የፌደራል መንግስትም የተናጠል ተኩስ አቁም የተፈለገውን ለውጥ አላመጠም በማለት መከላከያና የክልል ልዩ ሃይሎች እርምጃ እንዲወስዱ ትእዛዝ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ መንግስት ህወሃት በወረራቸው አካባቢዎች ግድያና መጠነ ሰፊ ዘረፋ ፈጽሟል በማለት ይከሳል።
በመንግስት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሃት ግን በሁለቱ ክልሎች ጥቃት መፈጸሙን አምኖ፤ በንጹሃን ላይ ጥቃት አድርሷል የሚለውን ክስ እያስተባበለ ይገኛል።