አሜሪካ፤ ኢትዮጵያ የተመድ ሰራተኞችን በተመለከተ ያሳለፈችው ውሳኔ “እንዲቀለበስ” ጥሪ አቀረበች
የጸጥታው ምክር ቤት እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አባላት አስቸኳይ እርምጃን እንዲወስዱም ጠይቃለች
ዋሽንግተን ይህ የማይሆን ከሆነ ወሳኝ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንደማታቅማማ አሳስባለች
አሜሪካ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች መባረርን በተመለከተ በኢትዮጵያ መንግስት የተላለፈው ውሳኔ “እንዲቀለበስ” ጥሪ አቀረበች፡፡
ኢትዮጵያ “ወሳኝ የሰብዓዊ እርዳታ ስራዎችን የሚሰሩ ሰባት የተመድ ሰራተኞችን ለማባረር መወሰኗን በጥብቅ እናወግዛለን” ያሉት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን ውሳኔው እንዲቀለበስ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“ኢትዮጵያ የተመድን ሰራተኞች ለማባረር መወሰኗን በመስማቴ ደንግጫለሁ”-አንቶኒዮ ጉቴሬዝ
ይህ የማይሆን ከሆነ አሜሪካ ጠንካራ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንደማታቅማማ ነው ብሊንከን ያሳሰቡት፡፡
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደርም በነጩ ቤተመንግስት (ኋይት ሃውስ) በኩል “ያልተጠበቀ” ያለውን የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ በማውገዝ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው “እርምጃው በጋራ ፍላጎቶቻቸው ላይ የተቃጣ ነው” ያለ ሲሆን “መቆም አለበት” በሚል ከተመድ አመራሮች ጋር መስማማቱን አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል ያለቻቸውን 7 የተመድ ሰራተኞች በ72 ሰዓታት ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አሳሰበች
እርምጃውን ተከትሎ “በሰሜናዊ ኢትዮጵያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለርሃብ መጋለጣቸውን የሚያሳዩ ሪፖርቶች እየወጡ ነው”ም ነው አስተዳደሩ በመግለጫው ያለው፡፡
“የኢትዮጵያ መንግስት ምግብ እና መድሃኒቶችን ጨምሮ ሌሎች ሰብዓዊ እርዳታዎችን ለማደናቀፍ የሚያደርገው ጥረት አካል እንዳይሆን ሰግተናል” ሲልም አስቀምጧል፡፡
የጸጥታው ምክር ቤት እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አባላት፤ ሰብዓዊ እንቅስቃሴዎችን በማስተጓጎል የራስን ዜጎች የህልውና መሰረቶች መንፈግ ተቀባይነት እንደሌለው አስቸኳይ እርምጃዎችን በመውሰድ ለኢትዮጵያ መንግስት በግልጽ እንዲያሳዩም ጠይቋል፡፡
ፕሬዝዳንት ባይደን በሰሜኑ ግጭት ተዋናዮች ላይ የገንዘብ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችለውን የውሳኔ ሀሳብ በፊርማቸው ማጽደቃቸውን በማስታወስም ይህን በመጠቀምም ሆነ በሌሎች መንገዶች ሰብዓዊ እርዳታዎችን ለሚያስተጓጉሉ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠትና እርምጃ ለመውሰድ አናቅማማም ብሏል፡፡