አይ ኦ ኤም፤ የኢትዮጵያ ዳይሬክተሩን ‘ያልተፈቀደ’ ቃለ መጠይቅ ማድረጋቸውን ተከትሎ ወደ ዋና መስሪያ ቤቱ ጠራ
ዋና ዳይሬክተሯ በቃለ መጠይቁ በድርጅቱ የበላይ አመራሮች ፊት መነፈጋቸውንና አመራሮቹ ለህወሓት የሚያደላ ልብ እንደላቸው ተናግረዋል
አይ ኦ ኤም፤ ማውሪን አሺዬንግ ረፍት ወጥተው በአስቸኳይ ወደ ዋና መስሪያ እንዲመጡ ነው ያደረገው
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ተቋም (አይ ኦ ኤም) የኢትዮጵያ ዳይሬክተሩን ማውሪን አሺዬንግን ጠራ፡፡
ድርጅቱ ማውሪን አቺዬንግ እረፍት እንዲወጡም አድርጓል፡፡
ይህን ያደረገው ከሰሞኑ ከሰጡት እና ‘ያልተፈቀደ’ ካለው ቃለ መጠይቅ ጋር በተያያዘ ነው፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ ከሰሞኑ ጄፍ ፒርስ ከተባለ ጸሃፊ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ በመንግስታቱ ድርጅት የበላይ አመራሮች ፊት መነፈጋቸውንና አመራሮቹ ለትግራይ አማጽያን የሚራራ የድጋፍ ልብ እንዳላቸው ተናግረው ነበር፡፡
ኢትዮጵያ የተመድ ሰራተኞች ላይ ባሳለፈችው ውሳኔ ዙሪያ ለማንኛውም አካል ማብራሪያ የመስጠት ግዴታ የለባትም- አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ
የትግራዩ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩ የድርጅቱ አመራሮች መሬት ላይ ያለውን ነገር በውል ለሚያውቁ ሰራተኞች ጆሮ ለመስጠት አለመፈለጋቸውንም ነው ዋና ዳይሬክተሯ የተናገሩት፡፡
ይህን ተከትሎ አቺዬንግ እረፍት እንዲወጡ ተደርጎ ስዊዘርላንድ ወደሚገኘው የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት ተጠርተዋል፡፡
ይህንንም ኤ.ኤፍ.ፒ አግኝቼዋለሁ ባለውና ትናንት ሰኞ የተጻፈ ነው ባለው ደብዳቤ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
በቃለ መጠይቁ ስለ ህወሓት ጨካኝነት መናገራቸውን ጭምር በዘገባው ያሰፈረው ኤ.ኤፍ.ፒ ወደ ትግራይ ላለመመለስ ቃል ገብተዋልም ይላል።
ህወሓት ከሳዑዲ አረቢያ የተባረሩ ትግራዋይ ስደተኞች ወደ ሩዋንዳ እንዲጓዙ ለማድረግ ሲያሻጥር እንደነበርም ነው አቺዬንግ የሚናገሩት፡፡
“እናም ከሩዋንዳ ምን ዐይነት የሽምቅ ውጊያ እንደሚጀመር አላውቅም፤ ማለቴ እንዲህ ዐይነት ነገር ቆሻሻ ነው” ሲሉም አስቀምጠዋል።
አይ ኦ ኤም ግን ይህን የአቺዬንግን ወቀሳ አስተባብሏል፡፡ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አንቶኒዮ ቪቶሪኖ በጻፉት የማስተባበያ ደብዳቤ ቃለ መጠይቁ በምንም ዐይነት መልኩ ድርጅቱን እንደማይወክል ገልጸዋል፡፡
ደብዳቤው ስም አይጠቅስም፡፡ ሆኖም ተጠያቂዋ ረፍት ወስደው በአስቸኳይ ወደ ዋና መስሪያ ቤቱ እንዲመጡ መደረጉንና ምርመራ መጀመሩን ያስቀምጣል፡፡
የድርጅቱ የምስራቅ እና የአፍሪካ ቀንድ አስተባባሪ በበኩላቸው አቺዬንግ ከተቋማዊ መርሆዎች ያፈነገጠ ድርጊት መፈጸማቸውን ለኤ.ኤፍ.ፒ ተናግረዋል፡፡
ስራቸውን በገለልተኛ ለመስራት እንደሚጥሩም ነው አስተባባሪው የተናገሩት፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክረታሪያት ቢል ለኔ ስዩም በበኩላቸው እውነታውን በተናገሩት አቺዬንግ ላይ የተደረገውን ነገር አውግዘዋል፡፡
ከህወሓት ጋር በተያያዘ በተመድ ውስጥ ያለውን ተቋማዊ አድልዎ ማጋለጣቸውን ተከትሎ ይህ መደረጉ “የሚረብሽ” እንደሆነም ነው ፕሬስ ሴክረታሪያቷ በይፋዊ የትዊተር የማህበረሰብ ገጻቸው የጻፉት፡፡
ቢል ለኔ በድርጅቱ ከፍተኛ የስልጣን እርከኖች ያለው “ውጫዊ እና ውስጣዊ ተጽዕኖዎችን የማሳደር ፖለቲካ ሊመረመር ይገባዋል”ም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቅርቡ ሰባት የተመድ ሰራተኞችን ማባረሯ የሚታወስ ነው፡፡