ተመድ የዩክሬን እና ሩስያ ጦርነት እንዲቆም በሚጠይቅ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ድምጽ ሊሰጥ ነው
የውሳኔ ሀሳቡ የተዘጋጀው በአሜሪካ እና በዩክሬን መሆኑ ተነግሯል

ጦርነቱን ለማስቆም ዋሽንግተን በጀመረችው ጥረት የአሜሪካ እና የሩስያ ከፍተኛ ባለስልጣናት በዚህ ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚገናኙ መዘገቡ ይታወሳል
በሩስያ እና ዩክሬን መካከል የሚደረገው ጦርነት እንዲቆም የሚጠይቁ የውሳኔ ሀሳቦች ላይ የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ድምጽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዕለቱ የጸጥታው ምክር ቤት አሜሪካ በምታቀርበው የጦርነት ማቆም የውሳኔ ሀሳብ ላይ ድምጽ እንደሚሰጡ የአሜሪካ ድምጽ ዘግቧል፡፡
ዋሽንግተን ባዘጋጀችው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ጦርነቱ በአፋጣኝ እንዲቆም እና በዩክሬን እና በሩስያ መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጠይቃለች፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የውሳኔ ሀሳቡ የጦርነቱን አስከፊነት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ግጭቱን በማስቆም የራሱን ሚና እንዲጫወት የሚያሳስብ ነው ብለዋል፡፡
በዩክሬን የተዘጋጀው የውሳኔ ሀሳብ በበኩሉ “ለሶስት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት ለዩክሬን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ቀጠናዎች እና ለአለም አቀፍ መረጋጋት አስከፊ እና ዘላቂ መዘዝ ማስከተሉን” አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም እየተጠናከረ የሚገኘው የሩስያ ጥቃት በአፋጣኝ እንዲቆም የጦርነቱ በዚህ አመት መጠናቀቅ ያለውን አስፈላጊነት ገልጿል።
የዩክሬን ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ የሩስያ ጦር ከዩክሬን አለም አቀፍ እውቅና ካገኘችባቸው ድንበሮች ሙሉ ለሙሉ እንዲወጣ የሚጠይቀውን ጨምሮ ቀደም ሲል በጠቅላላ ጉባኤው የተላለፉ ውሳኔዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆን አለባቸው ብሏል፡፡
የጠቅላላው ጉባኤ ውሳኔዎች አስገዳጅ ባይሆኑም የአለም አቀፉን ማህበረሰብ የሞራል ጥያቄዎች የሚያስተጋቡ እንደሆኑ ይነገራል፡፡
በፀጥታው ምክር ቤት አንድ የውሳኔ ሃሳብ ተግባራዊ ለመሆን ከ15 አባላት ቢያንስ የዘጠኙን ድጋፍ ሊያገኝ ይገባል፡፡
ከዚህ ባለፈም የትኛውም ቋሚ አባላት ብሪታንያ ፣ ቻይና ፣ ፈረንሳይ ፣ ሩሲያ እና አሜሪካ ውሳኔውን ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት በመጠቀም አለመሻር ይኖርባቸዋል፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በዚህ ሳምንት በዋሽንግተን በሚያደርጉት ጉብኝት የአውሮፓን የዩክሬን የሰላም እቅድ ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ፕሬዝዳንት ማክሮን ከጉብኝቱ ቀደም ብሎ “የአሜሪካ መሪ በሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ፊት ደካማ ሆኖ መታየት እንደሌለበት እነግራቸዋለሁ” ብለዋል፡፡
የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ሶስተኛ አመቱን ባስቆጠረበት በዛሬው ዕለት ኪየቭ ከ185 የሞስኮ ድሮኖች መካከል 113ቱን መታ መጣሏን አስታውቃለች፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ እና የሩስያ ባለስልጣናት ጦርነቱን ለማስቆም በጀመሩት ውይይት በዚህ ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ ተገናኝተው ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡