የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለዶ/ር ኢሌኒ ሰጥቶ የነበረውን የክብር ዶክትሬት ሰረዘ
የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት "ክብር ለሚገባው ክብርን መስጠት ብቻ ሳይሆን፤ በሙያው ላልታመነና አገሩን ለከዳ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ መለመድ አለበት!" ሲሉ ገልጸዋል
ዶ/ር ኢሌኒ ሰሞኑን በድብቅ በተዘጋጀ የበይነመረብ ስብሰባ ላይ ከዋና ዋና እሴቶቹ የሚፃረር ሀሳብን ማራመዳቸውን ዩኒቨርስቲው አስታውቋል
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሴኔት የኢትዮጵያ ምርት ገበያን በማቋቋምና በመምራት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሰኔ 29 ቀን 2005 ዓ.ም ለዶ/ር ኢሌኒ ዘውዴ ገብረ መድኅን ሰጥቶት የነበረውን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ (Honorary Degree of Humane Letters (DHLitt)) መሰረዙን አስታወቀ።
በወቅቱ የክብር ዶክትሬቱ የተሰጣቸው "የህብረተሰባችንን አኗኗር እና የሀገራችን የውጭ ንግድ ስርዓት እንዲሻሻል ባበረከቱት መልካም አስተዋጽኦ እና ለወደፊቱም በተሰጣቸው የክብር ዶክትሬት ልክ ሀገራችን ያለ አድሎና በእኩልነት እንዲሁም የዩኒቨርሲቲያችንን ራዕይ፣ ተልዕኮና እሴቶች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አምባሳደር ሆነው እንዲያገለግሉ" በማሰብ ነበር ያለው የዩኒቨርሲቲው ሴኔት "ይሁን እንጅ ዶ/ር ኢሌኒ ሰሞኑን የዓለም አቀፍ ሰላምና ልማት ማዕከል ተብሎ ይጠራ በነበረው ድርጅት አማካኝነት በድብቅ በተዘጋጀ የበይነመረብ ስብሰባ ላይ ሙያዊነትን ያልጠበቀ፣ አድሏዊ፣ የአንድን ቡድን ፍላጎት ብቻ ያንጸባረቀ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲያችንን ዋና ዋና እሴቶች (ሙያተኝነት፣ ትብብር፣ ማህበራዊ ኃላፊነት፣ ብዝኀነትና አካታችነት) የሚፃረር ሀሳብን" ማራመዳቸውን ገልጿል።
በዚህም ጉዳዩን በድጋሚ ሲያጤን እና ሲመረምር መቆየቱን የገለጸም ሲሆን የዩኒቨርስቲው ሴኔት ዛሬ ማክሰኞ ህዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ ሰጥቶት የነበረውን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ እንዲሰረዝ መወሰኑን አስታውቋል።
የክብር ዶክትሬት የሚሰጠው "አንድ ሰው ባለፈው ለሠራው ተቋማዊ፣ አገራዊና ዓለማቀፋዊ አበርክቶ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም በሙያው የሚጠበቅበትን የበለጠ ተግቶ እንዲሠራ ጭምር በማሰብ ነው" ያሉት የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት አስራት ዓፀደወይን (ዶ/ር) "ባለፈው ለሠራው እውቅናና ሽልማት ለወደፊቱ ቀብድ ማለት ነው። ሲከበር የበለጠ አገሩንና ሙያውን እንዲያከብር ነው" ሲሉ በማህበራዊ ገጻቸው አስፍረዋል።
ፕሬዝዳንቱ "የዩኒቨርሲቲያችን የዛሬ ውሳኔ የተቋማችን ሴኔት ሌጅስሌሽን፣ የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መሠረት አድርጎ የተወሰደ ውሳኔ ነው" ያሉም ሲሆን "ክብር ለሚገባው ክብርን መስጠት ብቻ ሳይሆን፤ በሙያው ላልታመነና አገሩን ለከዳ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ መለመድ አለበት!" ሲሉ ገልጸዋል።