ተመድ በሰሜን ኢትዮጵያ ያሉ ዜጎችን ለመደገፍ የ338 ሚሊየን ዶላር እጥረት እንዳለበት ገለፀ
በትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች ያሉ አርሶአደሮች እርሻ ስራቸው እንዲመለሱ ምርጥ ዘርና ሌሎች ድጋፎችን እያደረገ ነው
በሰሜን ኢትዮጰያ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት 9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተረጅዎች መኖራቸውን ተመድ ገልጿል
የተባሩት መንግስታት ድርጅት በሰሜን ኢትዮጵያ ያሉ ዜጎችን ለመደገፍ የ338 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እጥረት እንዳለበት ገለጸ።
የተባሩት መንግስታት ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ ለአል-ዐይን በላከው መግለጫ በሰሜን ኢትዮጵያ 9 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎችን በመርዳት ላይ ነው።
ባለፉት ሳምንታት ውስጥም ጦርነቱ በተከሰተባቸው ትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ያሉ አርሶአደሮች ወደ ቀድሞ እርሻቸው እንዲመለሱ ምርጥ ዘር እና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
በግጭት ቀጠና ውስጥ ላሉ እነዚህ አርሶ አደሮች የአፈር ማዳበሪያ እና የጤና ድጋፎች ሊደረግላቸው እንደሚገባም ድርጅቱ አሳስቧል።
በአጠቃይ በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉ አካባቢዎች ያሉ እና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች 957 ሚሊየን ዶላር ያስፈልገኛል ያለው ድርጅቱ ከዚህ ውስጥ 338 ሚሊየን ዶላር እጥረት እንደገጠመውም አስታውቋል።
ድርጅቱ ከሶስቱ ክልሎች ባለፈ በጦርነቱ ምክንያት ወደ ጎረቤት ሀገር ሱዳን የተሰደዱ ከ60 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞን በመርዳት ላይ መሆኑንም አክሏል።
ከ18 ወራት በፊት የሀገር መከላከያ ሰራዊት እዞች መካከል አንዱ የሆነው ሰሜን እዝ በህወሃት ታጣቂዎች መጠቃቱን ተከትሎ ነበር በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተጀመረው።
በዚህ ጦርነት ምክንያትም 80 በመቶ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ህይወታቸው በእርዳታ ላይ ሲመሰረት፤ ህወሃት ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች አዲስ ጥቃት በመክፈቱ የተረጂዎች ቁጥር ሊያሻቅብ ችሏል።
የፌደራል መንግስት ወደ ትግራይ ክልል ያልተገደበ እርዳታ እንዲገባ በተስማማው መሰረት የዓለም ምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ ሌሎች ለጋሽ ተቋማት ለተረጂዎች የሚውሉ ምግብና መድሃኒት በመግባት ላይ ናቸው።