አሜሪካ፣ ተመድና አውሮፓ ፑቲን በዩክሬን ላይ የወሰዱትን የበቀል ጥቃት አወገዙ
አውሮፓ ህብረት፤ “እንደነዚህ ያሉት ድርጊቶች በ 21 ኛው ክፍለ ዘመን ምንም ቦታ የላቸውም” ብለዋል
የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በሩሲያ የአየር ጥቃት “ኩፉኛ ደንግጫለሁ” ብለዋል
አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረት ሩሲያ በዩክሬን ላይ የወሰደችውን የበቀል ጥቃት አወገዙ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዩክሬን በሚገኙ ከተሞች ላይ በሩስያ የተፈጸመው የሚሳኤል ጥቃትን አሜሪካ "በጽኑ ታወግዛለች" ብሏል።
ድረጊቱ የቭላድሚር ፑቲንን በዩክሬን ህዝብ ላይ ያለው "ፍጹም ጭካኔ" ያሳያል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ መንግስታቸው ለዩክሬን የሚያደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከዩክሬኑ አቻቻው ዘለንስኪ ጋር በነበራቸው የስልክ ንግግር ቃል ገብተዋል።
ባይደን በተለይ ዩክሬን ከእንዲህ ዓይነቱ ጥቃት ራሷን መከላከል የሚያስችላትን የአየር መቃወሚያ ከአሜሪካ እንዲመሰጣት ቃል ገብተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በሩሲያ የአየር ጥቃት “ኩፉኛ ደንግጫለሁ” ማለታቸው የተናገሩት ደግሞ የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ናቸው።
ዋና ጸሃፊው ጥቃቱ ተቀባይነት የሌለው፣ ጦርነቱን የሚያባብስና እንደ ሁልጊዜም ሲቪሎች ከፍተኛውን ዋጋ እየከፈሉ ያሉበት አሳዣኝ ድርጊት ነውም ብለዋል።
የአውሮፓ ኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን ሩሲያ በዩክሬን ላይ የደረሰው ጥቃት "አስደንጋጭ" መሆኑን ሲገልጹ፤ የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርለስ ሚሼል በበኩላቸው የሩስያ ድርጊት “የጦር ወንጀል ነው” በማለት ፈርጀውታል።
የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካዩ ጆሴፕ ቦሬል በበኩላቸው፤ በኪቭ እና በዩክሬን ውስጥ ባሉ ሌሎች ከተሞች በሲቪሎች ላይ ሩሲያ ባደረሰችው ጥቃት በጣም መደንገጣቸው ተናግረዋል።
“እንደነዚህ ያሉት ድርጊቶች በ 21 ኛው ክፍለ ዘመን ምንም ቦታ የላቸውም” ሲሉም በትዊትር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ አጋርተዋል።
ቻይናና ህንድ ከሌሎቹ በተለየ መልኩ ሁለቱም ወገኖች ሁኔታዎችን ከማባባስ እንዲቆጠቡ መክረዋል።
ትናንት መስከረም 30፣ 2015 ዓ.ም ሩሲያ በዩክሬን ከተሞች መጠነ ሰፊ ጥቃት መሰንዘሯ ይታወቃል።
ቭላድሚር ፑቲን የትናንቱ ጥቃት ዩክሬን ባለፈው ቅዳሜ በክሬሚያ ድልድይ ላይ ላደረሰችው “የሽብር ጥቃት” በቀል እርምጃ ነው ብለዋል።
ዩክሬን እንዳለችው ትናንት ብቻ ከሩሲያ 83 ሚሳኤሎች መተኮሳቸውን እና ከነዚህ ውስጥ 43 መቀልበሳቸውን ተናግራለች።
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ፤ሩሲያ የኢራንን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ጥቃት እያደረሰችብን ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
ጥቃቱ በተለያዩ የዩክሬን ከተሞች ላይ ያነጣጠረ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ የዩክሬን የኢነርጂ መሰረተ ልማቶችን ኢላማ ያደረገ እንደሆነም አስታውቀዋል።
የአሁን ተከታታይ የሰው አልባ አውሮፕላን ሚሳዔሎች ድብደባ የጦርነቱ መጀመሪያ አከባቢ ሞስኮ ኪቭን ለመቆጣጠር ታደርገው የነበረ መጠነ ሰፊ ጥቃት አይነት ነው ተብሏል።
“አንበገርም” የሚሉት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ጥቃቱን ተከትሎ ለህዝባቸው ባስተላለፉት የቪዲዮ መልእክት “እንዲህ ዓይነት ጥቃቶች ፍርሃት ውስጥ አይከቱንም፤ ይልቅ ይበልጥ ያጠናክሩናል” ሲሉም ተናግረዋል።
በትናንቱ ተከታታይ የሚሳኤል ጥቃት በትንሹ 14 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 97 የሚሆኑ ደግሞ ቆስለዋል።