ልዩልዩ
ፕሬዝዳንት ፑቲን ለአሜሪካዊው ተዋናይ ስቴቨን ሴጋል ከፍተኛ ብሄራዊ ሽልማት ሰጡ
ዩክሬን በብሄራዊ ደህንነት ምክንያት ሲጋል ለ5 ዓመታት ወደ ሀገሪቱ እንዳይገባ አግዳለች
ታዋቂው ተዋናይ "በሰብዓዊ ስራው" ሽልማቱን እንዳገኘ ተነግሯል
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሆሊውድ ተዋናይ ለሆነው ስቴቨን ሲጋል በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እና የባህል ስራው የሀገሪቱን ከፍተኛ ብሄራዊ ሽልማት ሰጥተዋል።
ሞስኮ ሽልማቱን በብሄራዊ ድንጋጌ ማሳተሟም ታውቋል።
ድንጋጌው የ 70 ዓመቱ ስቴቨን ሲጋል እንደ "አንደር ሲጂ" (በከበባ ስር) ባሉ የተግባር (አክሽን) ፊልሞች የሩስያን ጓደኝነት አሳይቷል ብሏል። ሮይተርስ እንደዘገበው ሴጋል እስካሁን ምንም ምላሽ አልሰጠም።
ድንጋጌው የሲጋልን ስራ 'ለአሜሪካ እና ጃፓን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የሰብዓዊ ልዩ ተወካይ' አድርጎ ጠቅሷል።
የአሜሪካ ተወላጅ የሆነው ተዋናይ እና የማርሻል አርት ባለሙያ በጃፓን ውስጥ ሰርቷል።
ፑቲንን ለረጅም ጊዜ ሲያደንቅ ቆይቷል የተባለው ተዋናይ በፈረንጆች 2016 የሩሲያ ፓስፖርት ተቀብሏል።
ሩሲያን አዘውትሮ በመጎብኘትም ይታወቃል። ሲጋል በ2014 የክሬሚያን ወደ ሩሲያ መጠቃለል በመደገፍ የሞስኮን አቋም "ምክንያታዊ" ብሎታል።
በቅርቡም በሩሲያ የተያዘውን የዩክሬን ምስራቃዊ ክፍል ጎብኝቷል። ዩክሬን በፈረንጆች 2017 በብሄራዊ ደህንነት ምክንያት ሲጋልን ለአምስት ዓመታት እንዳይገባ አግዳለች።