አሜሪካ እና ተመድ በትግራይ ጉዳይ የኢትዮጵያን ጥረት መደገፍ እንደሚቀጥሉ ገለጹ
በርካታ ድርጅቶች እና የሰብዓዊ ድጋፍ ሰራተኞች ወደ ትግራይ የመግባት ፈቃድ ማግኘታቸውን የሰላም ሚኒስቴር ገልጿል
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ከተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር በስልክ ተወያይተዋል
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር ትናንት በስልክ ባደረጉት የትውውቅ ቆይታ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረገጹ እንዳስታወቀው ፣ ሁለቱ ግለሰቦች ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለው ወቅታዊ ጉዳይ ይገኝበታል፡፡ ኢትዮጵያን በተመለከተው ውይይታቸው ፣ ሁለቱም በትግራይ ለተፈጠረው ቀውስ ምላሽ ለመስጠት የኢትዮጵያን ጥረት ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡
ሚስተር ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በቅርቡ በነበራቸው የስልክ ውይይት ወቅትም በትግራይ ክልል መንግስት የሚሰራውን ስራ አሜሪካ እንደምትደግፍ ገልጸው ሰብዓዊ ድርጅቶች በክልሉ እንዲንቀሳቀሱ መንግስት ሙሉ ፈቃድ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
በመከላከያ ሰራዊት እና በሕወሓት ኃይል መካከል በትግራይ ክልል የተካሔደው ውጊያ በርካታ ቀውሶችን ማስከተሉ ይታወቃል፡፡ ከነዚህም መካከል የንጹኃን መፈናቀል እና የሰብአዊ ቀውስ ይገኙበታል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም በክልሉ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና መደረግ ያለባቸውን ተግባራት በተመለከተ ሪፖርቶችን አውጥተዋል፡፡
የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅቶች ያለምንም ገደብ ወደ ክልሉ እንዲገቡ እና ድጋፍ እንዲያደርሱ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የተለያዩ መንግስታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጫና ሲያሳድሩ ቆይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከሰብዓዊ ድርጅቶች ጋር በደረሰው ስምምነት መሰረት የተለያዩ ድርጅቶች ወደ ክልሉ ገብተው በመስራት ላይ መሆናቸው በተለያዩ ጊዜያት ይፋ ሆኗል፡፡ የሰላም ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል የሰላም ማስከበር ሂደቱን ተከትሎ ላለፋት 3 ወራት የተባበሩት መንግስታት ልዩ ልዩ ድርጅቶችን ጨምሮ ከ26 በላይ አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በጥምረት የሰብዓዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ተግባራን ለማገዝ ሰፊ እንቅስቃሴ ሲደረግ እንደቆየ አስታውቋል፡፡
ባለፉት 3 ወራት በቦታው ተገኝተው ድጋፍ ለማድረግ ላመለከቱ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ዓለም አቀፍ መመዘኛን አሟልተው ለተገኙ 75 አባላት ወደ ትግራይ ክልል በመግባት የሰብዓዊ ድጋፍ ሂደቱን እንዲያግዙ ፈቃድ መስጠቱንም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ የኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት (UN-OCHA) የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፉንና የመልሶ ማቋቋም ሂደቱን በማስተባበር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅንጅት እያሰራ ይገኛልም ብሏል መግለጫው።
ከኢትዮጵያ ጉዳይ በተጨማሪ በሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይም የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የተመደወ ዋና ፀሐፊ ተወያይተዋል፡፡ አሜሪካ ወደ ዓለም ጤና ድርጅት መመለሷን እንዲሁም በኮሮና ቫይረስ ፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና መሰል ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ከተባበሩት መንግስታት እና በስሩ ከሚገኙ ድርጅቶች ጋር በትብብር እንደምትሰራ ብሊንከን ለጉተሬዝ አረጋግጠዋል፡፡