አሁንም ያልተቆራረጡ ሰብዓዊ ድጋፎች እንዲኖሩ ዋና ጸሃፊው አሳስበዋል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በትግራይ ያለው ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው ገለጹ፡፡
ጉቴሬዝ በቃል አቀባይ ጽህፈት ቤታቸው በኩል ባወጡት መግለጫ ድርጅታቸው አስቸኳይ ሰብዓዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት በኢትዮጵያ ጽህፈት ቤቱ በኩል ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለውን ጥብቅ ትስስር ጠቃሚነት አንስተዋል፡፡
አሁንም ለችግር የተጋለጡትን ለመጠበቅ እና ሰብዓዊ ሁኔታዎችን ለማቅለል ቀጣይነት ያላቸው አስቸኳይ እርምጃዎች እንደሚያስፈልጉ ነው ዋና ጸሃፊው አስምረው የተናገሩት፡፡
ጉቴሬዝ በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት ከሰሞኑ ጉብኝት ያደረጉትን የድርጅቱን ከፍተኛ አመራሮች ተቀብሎ ያስተናገደበትን አዎንታዊ ሁኔታ አድንቀዋል፡፡
አመራሮቹ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስለ ሁኔታው የጎበኙት ዋና ጸሃፊው በተጎዱ የክልሉ አካባቢዎች፣ለሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ለመጠለያ ጣቢያዎች ያልተቆራረጠ እና ዘላቂ ሰብዓዊ አቅርቦት እንዲኖር ለመንግስት ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ነው፡፡
ከሰሞኑ የድርጅቱ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ እና የደህንነት ዋና ጸሀፊ ጊልስ ሚካድ ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፡፡
በተለይ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ከሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ጋር በመሆን ትግራይ ክልል የሚገኘውን የማይ ዐይኒ የኤርትራውያን ስደተኞች መጠለያ ጣቢያን መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡
የዓለም ምግብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢዝሌይ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንደነበርም አይዘነጋም፡፡