አሜሪካ ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የ23 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያዎችን ልትሸጥ መሆኗን አስታወቀች
የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነቱ በዘመነ ትራምፕ የተደረሰ ነው
ሽያጩ ይፋ የሆነው ፕሬዝደንት ባይደን ለዩኤኢ የጦር መሳሪያ እንይሸጥ የተጣለውን እገዳ በማንሳታቸው ነው
አሜሪካ ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች 23 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ልትሸጥ መዘጋጀቷን አስታውቃለች፡፡
ይህ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነት በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የአስተዳድር ጊዜ የተጀመረ ቢሆንም በየመን ባለው ቀውስ ምክንያት እንዲዘገይ የተደረገ ነበር።
የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነቱ እንዲዘገይ የተደረገው በሳዑዲ አረቢያ መሪነት በየመን በተካሄደው ጦርነት ዩኤኢ መሳተፏን ተከትሎ ለተፈጠረው የሰብዓዊ ቀውስ ተጠያቂ ናቸው በሚል የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቋማት ባስነሱት ተቃውሞ ምክንያት ነበር።
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ፣ በትራምፕ የአስተዳደር ዘመን ከመካከለኛው ምስራቅ አገራትጋር የተደረጉ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነቶች እንዲዘገዩ አድርገዋል።
ፕሬዝደንቱ አሁን ላይ ፣ ለጊዜው እንዲዘገይ ተደርጎ የነበረው ለዩኤኢ የ23 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ እንዲቀጥል መወሰናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሮይተርስ እንደዘገበው ለተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ይሸጣሉ ከተባሉ የጦር መሳሪያዎች መካከል ኤፍ-35 የተሰኘው የጦር ጄት ፣ ተዋጊ ድሮኖች እና ሌሎች ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ይገኛሉ።
በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ዘመን ፀድቆ የነበረው የጦር መሳሪያ ሽያጭ በ ጆ ባይደን ታግዶ ከቆየ በኋላ አሁን ላይ እገዳው ተነስቷል፡፡