አዲሱ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በመጪው ሳምንት ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ
ከመጪው ሰኞ ይጀምራል የተባለው የልዩ መልዕክተኛው ጉብኝት እስከ ፈረንጆቹ ጥር 20 እንደሚዘልቅም ነው የተነገረው
ዴቪድ ሳተርፊልድ ሱዳንን ጨምሮ ሳዑዲ አረቢያን እንደሚጎበኙም ይጠበቃል
አዲሱ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሱዳን እና ሳዑዲ አረቢያን ሊጎበኙ ነው ተባለ፡፡
ሳተርፊልድ ከፈረንጆቹ ጥር 17-20 ባሉት ቀናት ነው ሃገራቱን የሚጎበኙት፡፡ በቅድሚያ ወደ ሪያድ እንደሚጓዙ የሚጠበቁት ልዩ መልዕክተኛው ቀጥሎ ካርቱምንና አዲስ አበባን ይጎበኛሉ ተብሏል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ረዳት ጸሃፊ ሞሊ ፊ አብረዋቸው ወደ ሃገራቱ እንደሚጓዙም ነው ከመስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ የሚያመለክተው፡፡
በሪያድ በሱዳን ያለው ወታደራዊ አገዛዝ እንዲያበቃ የሚጠይቁ የለውጥ ኃይሎችን እንደሚያገኙና በመንግስታቱ ድርጅት አመቻችነት ለማካሄድ ስለታሰበው ሃገራዊ ውይይት እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል፡፡
ወደ ካርቱም ተጉዘውም ከተለያዩ የለውጥና የዴሞክራሲ ኃይሎች ጋር እንዲሁም ከወጣት አደረጃጀቶች ጋር ይወያያሉ፡፡
በኢትዮጵያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር እንደሚወያዩም ይጠበቃል፡፡
መንግስት የተገኘውን የሰላም ጭላንጭል እንዲያጠናክር፣ የአየር ጥቃቶችን እንዲያቆምና ሌሎች መቃቃሮች እንዲያበቁ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚነጋገሩም ነው የተገለጸው፡፡
ተኩስ እንዲቆም፣ እስረኞች አሁንም እንዲለቀቁና ሰብዓዊ እርዳታዎች ሳይስተጓጎሉ እንዲቀርቡ ይጠይቃሉም ተብሏል፡፡
ዴቪድ ሳተርፊልድ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ከሌሎች የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር የተወያዩትን አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማንን ተክተው በቅርቡ በአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛነት መሾማቸው ይታወሳል፡፡
በተለያዩ በተለይም በእርስበርስ ጦርነትና እሰጣገባ ውስጥ ባሳለፉ ሃገራት ሃራቸውን በከፍተኛ ዲፕሎማትነት ያገለገሉት ሳተርፊልድ ፌልትማንን እስከተኩበት ጊዜ ድረስ በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር ነበሩ፡፡