“መንግስት ከህወሓት ጋር ተደራደር ቢባል እንኳን ‘ህዝቤ አይፈቅድልኝም’ ማለት አለበት”- ባልደራስ
መንግስት “የጦርነቱ እና የህወሓት ዋና ቀያሾች”ን ከእስር መልቀቁ የህግ የበላይነትን የጣሰ ነው ሲልም ተቃውሟል
ባልደራስ አመራሮቹ እና አባላቱ የተከሰሱት “በሀሰት” መሆኑን ገልጾ መንግስት ይቅርታ ጠይቆ ካሳ ሊከፍላቸው ይገባል ብሏል
መንግስት “ከህወሓት ጋር ተደራደር ቢባል እንኳን ህዝቤ አይፈቅድልኝም” ማለት እንዳለበት ባልደራስ ለእውነት ዴሞክራሲ ፓርቲ አሰታወቀ።
ፓርቲው ከፍተኛ አመራሮቹ ከተፈቱ በኋላ የመጀመሪያውን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የፓርቲው ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋ መንግስት የሀገርን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል ውሳኔ መወሰን እንደሌለበት ገልጸዋል።
መንግስት ከህወሓት ጋር ለመደራደር ቢቀመጥ “ህዝቤ አይፈቅድልኝም” ማለት እንዳለበትም ፓርቲው ገልጿል።
ባልደራስ አመራሮቹና አባሎቹ የተከሰሱት “በሀሰት” መሆኑን ገልጾ መንግስት ይቅርታ ጠይቋቸው፤ ካሳ ሊከፍላቸው ይገባልም ብሏል። ፕሬዝዳንቱ አቶ እስክንድር ነጋ የገለጹትም ይኼንኑ ነው፡፡
“በሃሰት ተከሰው የታሰሩትን የባልደራስ አመራሮችና አባላት መንግስት ይቅርታ ሊጠይቅና ካሳ ሊከፍላቸዉ ይገባል” ሲሉም ተናግረዋል በመግለጫው፡፡
ባልደራስ ከተመሰረትኩበት ጊዜ አንስቶ ገዢዉ ፓርቲ “ብርቱ በትር ሲያሳርፍብኝ” ነበርም ብሏል፡፡
የህወሓት የጦርነቱና የፖለቲካ ዋና ቀያሾች የሆኑ እስረኞች ከእስር መዉጣት መጀመራቸዉ የህግ የበላይነትን የጣሰ ዉሳኔ መሆኑንም ባልደራስ አስታዉቋል፡፡
መንግስት ምዕራፍ አንድ ያለዉን ዘመቻ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሳያረጋግጥ ማቆሙ “ትልቅ አደጋ ያዘለ” መሆኑንም ነው፤ “ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሬ መታገሌን እቀጥላለሁ” ያለው ባልደራስ የገለጸው፡፡
ይደረጋል የተባለው የምክክር ሂደትን በተመለከተ ባለቤቱ ህዝብ፣ የፖለቲካ ኃይሎችና የሲቪክ ተቋማት መሆናቸውን በማስታወስም ሂደቱ ሁሉም ባለድርሻዎች በባለቤትነት እንዲመሩት ጠይቋል፡፡
የምክክሩ ቅድመ ሁኔታ የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት መሆን አለበት ያለው ባልደራስ በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስን ያለ ቅድመ ሁኔታ መቀበል ይገባል ሲል ጥሪ አቅርቧል።
ባልደራስ የሰሜኑ ጦርነት ህወሓት በጀመረው ቅድመ ማጥቃት መቀስቀሱን እንደሚያምንም አስታውቋል።