
ልዩ መልዕክተኛው አዲስ አበባ ገብተዋል
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ በመሆን የተሾሙት ዴቪድ ሳተርፊልድ ዛሬ ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር እንደሚገናኙ ተገለጸ።
ዴቪድ ሳተርፊልድ እና የኢትዮጵያ መንግስት ባለስጣናት የሚገኛኙት በአዲስ አበባ ነው ተብሏል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንዳስታወቀው ልዩ መልዕክተኛው ከመንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ በኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ከአፍሪካ ህብረት አመራሮች፤ ከሰብዓዊ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።
የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ በአራት ክልሎች ጉብኝት በማድረግ ወደ አሜሪካ መመለሳቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት በሰላም ለመፍታት ንግግሮች መቀጠላቸውን ገልጸው ነበር።
የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛም በዚሁ የአዲስ አበባ ቆይታቸው በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት በሰላም በሚፈታበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
ሳተርፊልድ በዚህ ኃላፊነታቸው ከተሾሙ በኋላ ባለፈው ወር አዲስ አበባ መምጣታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ሳተር ፊልድ ባለፈው ወር በአዲስ አበባ አድርገውት በነበረው ጉብኝት ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳፋኪ ጋር ተገናኝተው ነበር።