በየመን የተፈጸመው ጥቃት የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት አድማሱን እያሰፋ መሄዱን አመላክቷል
አሜሪካ እና ብሪታንያ በየመን የሃውቲ ታጣቂዎች ይዞታዎች ላይ ጥቃት አደረሱ።
ከደርዘን በላይ ይሆናሉ የተባሉት ጥቃቶች በአውሮፕላን እና ከመርከቦች ላይ በተተኮሱ ሚሳኤሎች አማካኝነት የተፈጸሙ ናቸው ተብሏል።
የአየር ድብደባው በሰንአ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ፣ በሆዴይዳ የሃውቲ ባህር ሃይል ጣቢያ እና በታይዝ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ መፈጸሙን ሬውተርስ የአይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።
በካንሰር ተጠቅተው ሆስፒታል የሚገኙት የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ሊዩድ ኦስቲን፥ በየመን የተፈጸሙት ጥቃቶች የሃውቲዎችን የድሮን፣ የባላስቲክና ክሩዝ ሚሳኤሎች እንዲሁም የአየር ቅኝት ራዳሮች ኢላማ ያደረጉ ናቸው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የየመኑ ታጣቂ ቡድን በቀይባህር የሚፈጽመውን ጥቃት ካላቆመ ሀገራቸው ተጨማሪ እርምጃ ለመውሰድ እንደማታመነታ ተናግረዋል።
የብሪታንያ መከላከያ ሚኒስቴርም “ሃውቲዎች በንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት የመፈጸም አቅማቸውን ለማዳከም እርምጃ መውሰዳችን እንቀጥላለን” የሚል መግለጫ አውጥቷል።
ኢራን በበኩሏ አሜሪካና ብሪታንያ ከአየርና ባህር ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን በየመን ላይ ማድረሳቸውን በጥብቅ አውግዛለች።
በቴህራን የሚደገፈው የየመኑ ታጣቂ ቡድንም አሜሪካና አጋሮቿ ዋጋ የሚከፍሉበትን ጥቃት መፈጸማቸውን በመጥቀስ በቀይ ባህር ወደ እስራኤል ጉዞ በሚያደርጉ መርከቦች ላይ ጥቃቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ሩሲያ የጸጥታው ምክርቤት በየመን ስለተፈጸሙት የአየር ድብደባዎች አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደርግ ጠይቃለች።
ሳኡዲ አረቢያም ውጥረት ከሚያባብሱ እርምጃዎች መታቀብ እንደሚገባ የሚያሳስብ መግለጫን አውጥታለች።
ከፈረንጆቹ 2016 ወዲህ በየመን የተፈጸመው የአየር ድብደባ የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት አድማሱን እያሰፋ መሄዱን አመላክቷል።
ዋሽንግተን ምንም እንኳን ውጥረቱን ማባባስ እንደማትፈልግ ብትገልጽም በየመን ከ12 በላይ የአየር ድብደባዎችን መፈጸሟ ሃውቲዎችን እና ቴህራንን አስቆጥቷል።
ለዋሽንግተን እና ለንደን የሰንአ ድብደባ ከህዳር ወር ወዲህ በቀይ ባህር በሚጓዙ መርከቦች ላይ 27 የጥቃት ሙከራዎችን ያደረገው የሃውቲ ታጣቂ ቡድን የሚሰጠው አጻፋዊ ምላሽ ውጥረቱን ይበልጥ እንደሚያባብሰው ይጠበቃል።