አሜሪካ፤ የቻይናው ፕሬዝዳንት ፑቲን ላይ ጫና እንዲፈጥሩ ጠየቀች
የቻይናው ፕሬዝዳንት የሞስኮ ጉብኝት ለአሜሪም ሆነ አጋሮቿ ምቾት ያልሰጠ ጉዳይ መሆኑ እየተገለጸ ነው
የቻይና ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠውን ጉብኝት ለማድረግ ሞስኮ ናቸው
አሜሪካ፤ ለጉብኝት ሞስኮ የሚገኙት የቻይናው ፕሬዝዳንት የዩክሬን ጦርነት እንዲያበቃ ፑቲን ላይ ጫና እንዲፈጥሩ ጠየቀች፡፡
ፕሬዝዳንት ሺ የሩሲያው አቻቻው ፑቲን የዩክሬንን ሉዓላዊነት እንዲያከብሩ ሊነግርዋቸው ይገባልም ብላለች ዋሽንግተን፡፡
ይሁን እንጅ ቀድሞውኑ የቤጂንግን የዲፕሎማሲ አካሄድ በጥርጣሬ የምትመለከትው አሜሪካ የቻይናው መሪ የዩክሬንን ሉዓላዊነት ያላከበረ ሃሳብ እንዳያቀርቡ ስጋት እንዳላት ገልጻለች፡፡
የዋይት ሀውስ የብሄራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት በሞስኮ በጉብኝት ላይ የሚገኘትን ፕሬዝዳንት ሺ የሩሲያ ጦር በዩክሬን ሉዓላዊ ግዛት ባለበት ሁኔታ የተኩስ አቁም ጥሪን እንዳያቀርቡ ስጋት አለን ብለዋል፡፡የቻይናው መሪ በመጀመሪያ ደረጃ ጦርነቱ በዩክሬን ላይ ስለፈጠረው ጉዳት ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ጋር ቢነጋገሩ መልካም መሆኑን በመጠቆም፡፡
"ፕሬዝዳንት ሺ የዩክሬንን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን የማክበር አስፈላጊነት ላይ ፕሬዝዳንት ፑቲንን በቀጥታ እንዲጫኑ እናበረታታለን ፡፡ ጉዳዩ ዓለም እና የቻይና ጎረቤቶች በቅርብ የሚመለከቱት ነው"ሲሉም ተደምጠዋል የዋይት ሀውስ የብሄራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ፡፡
የቻይና ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠውን ጉብኝት ለማድረግ በትናንትናው እለት ሞስኮ መግባታቸው አይዘነጋም፡፡
ሺ ሞስኮ የገቡት የሩሲያ አቻቸው ፑቲን በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ በወጣባቸው ማግስት ነው።
በዚህም የቻይናው መሪ በዓለም አቀፉ ወንጀሎኞች ፍርድ ቤት (አይ ሲ ሲ) የእስር ማዘዣ የወጣባቸው የሩሲያው መሪ ፑቲንን ለመጀመሪያ ጊዜ እጃቸውን የጨበጡ የሀገር መሪ ሆነዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጉብኝቱ “ገደብ የለሽ ግንኙነት” እንዲኖራቸው ከስምምነት የደረሱት የሩሲያና ቻይና መሪዎች ተገናኝተው ሚመክሩበት እንደመሂኑ ለአሜሪካ እና ምዕራባውያን አጋሮቿ ትልቅ የራስ ምታት መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡
የሺ ጂንፒንግ ጉብኝት ደም አፋሳሹን የዩክሬን ጦርነት በንግግር እንዲቋጭ የጀመሩት ዲፕሎማሲዊ ጥረት አንዱ አካል ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡
ጉብኝቱ “የሰላም ጉዞ” የሚል ስያሜ እንደተሰጠውም ነው ተገለጸው፡፡
ቻይና የዩከሬን ጦርነት ለመቋጨት ያስችላል ያለችውን ባለ 12 ነጥብ ምክረ-ሃሳብ በማቅረብ ለዩክሬን ሰላም የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደቀተለች ነው፡፡
ይሁን እንጅ ዩክሬን እና አጋሮቿ የሚያቀርቡት ቅድመ ሁኔታ ሂደቱን አስቸጋሪ ሊያደርገው እንደሚችል ይገመታል፡፡
ዩክሬን እና ምዕራባውያን ደጋፊዎቿ የተኩስ አቁም ስምምነት የሩሲያው መሪ ይበልጥ እንዲዘጋጁና ጊዜ እንዲገዙ ከማድረግ ባለፈ ምንም ፋይዳ የለውም የሚል አቋም እንዳለቸው ይታወቃል፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ሩሲያ ከዩክሬን ግዛት ሙሉ በሙሉ ካልወጣች በቀር ምንም አይነት የድርድር ጥያቄ እንደማይቀበሉ በቅርቡ መግለጻቸውም አይዘነጋም፡፡
የሩሲያው መሪ ፑቲን በበኩላቸው ቻይና ጦርነቱ እንዲበቃ እየተጫወተችው ያለውን የአሸማጋይነት ሚና በደስታ እንቀበለዋለን ብለዋል፡፡
"በዩክሬን ጉዳይ ቻይና በያዘቸው ሚዛናዊ አቋም ደስተኞች ነን፤ ሀገሪቱ ቀውሱን ለመፍታት ገንቢ ሚና ለመጫወት ፈቃደኛ መሆኗን በደስታ እንቀበላለን”ም ብለዋል ፑቲን፡፡