በኢትዮጵያ እውነተኛ እና ተበዳዮችን ማዕከል ያደረገ የሽግግር ፍትህ ስርዓት እንዲሰፍንም ጠይቃለች
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከጸብ አጫሪነት ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሜሪካ አሳሰበች፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት የነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲቆም ምክንያት የሆነው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ አንድ ዓመት ሞልቶታል፡፡
የስምምነቱ አንደኛ ዓመት አስመልክቶ አሜሪካ ባወጣችው መግለጫ ስምምነቱ ጦርነቱ እንዲቆም ከማድረጉ በላይ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀድሞ ቤታቸው መመለስ መጀመራቸው እና ተቋርጠው የነበሩ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ማድረጉን ገልጻለች፡፡
ህወሃት ከባድ መሳሪያዎችን መመለስ መጀመሩ፣ ጊዜያዊ አስተዳድር መዋቀሩ፣ የሰብዓዊ ድጋፎች መቀጠላቸው፣ ተጎጂዎችን ለመካስ የሽግግር ፍትህ ስርዓት ለመዘርጋት ሂደት መጀመሩ በአንድ ዓመት ውስጥ የተፈጸሙ ዋና ዋና ጉዳዮች እንደሆኑም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ይሁንና የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ አሁንም ሙሉ ለሙሉ አልወጡም የሚለው የዋሸንግተን መግለጫ ሁለቱ ሀገራት አንዳቸው የአንዳቸውን ሉዓላዊነት እንዲያከብሩ፣ ከአላስፈላጊ ጸብ አጫሪነት ድርጊት እንዲታቀቡም አሳስቧል፡፡
አሜሪካ አክላም በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ሌሎች ክልሎች ያለው ግጭት እንዳሳሰባት ገልጻ እየተፈጸሙ ያሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ጥላቻዎች የሀገሪቱን እና አካባቢውን ወደ አለመረጋጋት የሚያስገፈባ ነውም ብላለች፡፡
ከአንታርክቲካ ድረስ እየመጡ ባለበት ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን መፈለጓ እንደ ስህተት መቆጠር የለበትም- የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር
ተበዳዮችን ማዕከል ያደረገ እና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን የሽግግር ፍትህ ስርዓት እንዲዘረጋም አሜሪካ አሳስባለች፡፡
እውነተኛ እና አሳታፊ ብሄራዊ ውይይት እንዲደረግ አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግም አስታውቃለች፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ መቀመጫቸው አዲስ አበባ ያደረጉ የ10 ሀገራት ኤምባሲዎች በኢትዮጵያ ለ2 ዓመታት ተካሂዶ በነበረው ግጭት ተሳትፈው የነበሩ ሁሉም ወገኖች የሰላም ስምምነቱን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
መግለጫውን ያወጡት ሀገራት አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ጃፓን፣ ኔዘርላንድስ፣ ኒውዚላንድ፣ ኖርዌይ፣ ስውዲን እና ብሪታንያ ናቸው፡፡