ዋሸንግተን “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት ወደ ሰላም መንድ ለመሄድ በር ይከፍታል” ብላለች
በኢትዮጵያ ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳቱን ተከትሎ በአዋጁ የታሰሩ ዜጎች እንዲለቀቁ አሜሪካ አሳሰበች፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱን በበጎ እንደሚመለከተው ገልጿል።
መንግስት አዋጁ እንዲነሳ ማድረጉ እየተካሄደ ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ተጨማሪ ጠቃሚ እርምጃ እንደሚሆንም ዋሸንግተን አስታውቃለች።
ይህ እርምጃም በአዋጁ የታሰሩ ሰዎችን በአስቸኳይ በመፍታት ሊቀጥል እንደሚገባም ነው የአሜሪካ መንግስት የጠየቀው።
ከጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት ሁሉን አቀፍ ምክክርን ለማፋጠንና ውጤታማ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ እንደሚያግዝ ዋሸንግተን አስታውቃለች።
አሜሪካ፤ ግጭት እንዲቆም፣ የሰብዓዊ አቅርቦት እዳይደናቀደፍ፣ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ ግልጽ ምርመራ እንዲደረግ የሚያስችል ንግግር ከሁሉም ወገኖች ጋር እንደምታደርግ አስታውቃለች።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ማጽደቁን ተከትሎ በእስር ላይ ያሉ ሰዎች እንዲለቀቁ ትናንት ምሽት መጠየቁ ይታወሳል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባሳለፍነው ጥር 18 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጊዜው ሳይደርስ ቀደም ብሎ እንዲነሳ ውሳኔ አሳልፎ ነበር። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በትናትናውአ ለት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለት የአስቸኳይ አዋጁ እንዲነሳ ወስኗል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመላው ኢትዮጵያ ከጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጎ ነበር።
አዋጁ ሚያዚያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም የሚያበቃ ቢሆንም ቀድሞ እንዲነሳ በመወሰኑ እንዲያጥር ተደርጓል።