የዩኤስኤይድ ድጋፍ በመቋረጡ በትግራይ ክልል ከ20 ሽህ በላይ ሰዎች ለአደጋ መጋለጣቸው ተነገረ
2.4 ሚሊየን ዜጎች ድጋፍ ጠባቂ በሆኑበት ክልል የኤጄንሲው ድጋፍ መቋረጥ የምግብ ዕጥረትን ሊያስከትል ይችላል ተብሏል

በ2023 በጀት አመት 1.8 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ያገኘችው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከዩኤስኤድ ከፍተኛ ድጋፍ በማግኘት ቀዳሚዋ ናት
በትግራይ በፌደራል መንግስት እና በክልሉ ኃይሎች መካከል የተደረገውን ጦርነት ተከትሎ በቀደመው ልክ ራሳቸውን መደጎም እና ማስተዳደር የማይችሉ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈጥረዋል፡፡
በጦርነቱ ከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ካስተናገዱ ክልሎች መካከል አንዱ የሆነው የትግራይ ክልል 2.4 ሚሊየን የሚጠጉ ዕርዳታ ጠባቂ ዜጎች መገኛ መሆኑን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ አለም አቀፍ የልማት ድርጅት ዩኤስኤይድ የስራ እንቅስቃሴ ለ90 ቀናት እንዲቋረጥ መወሰናቸውን ተከትሎ በርካታ የአለም ህዝቦች አደጋ የተጋረጠባቸው ሲሆን በመቀሌ እና አቅራቢያው የሚገኙ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም የዚሁ ስጋት ተካፋይ ናቸው፡፡
አሶሼትድ ፕረስ ከመቀሌ ወጣ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች የዩኤስኤይድ ድጋፍ በመቋረጡ ምክንያት 20 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ለአደጋ መጋለጣቸውን ዘግቧል፡፡
በ2023 በጀት አመት 1.8 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ያገኘችው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከዩኤስኤይድ ከፍተኛ ድጋፍ በማግኘት ቀዳሚ ስትሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ከዩክሬን ቀጥላ ሁለተኛዋ ናት፡፡
ገንዘቡ ከነፍስ አድን ምግብ በተጨማሪ ለኤችአይቪ መድሀኒት ፣ለክትባት ፣ለትምህርት ፕሮግራሞች ፣ ለስራ እድል ፈጠራ እንዲሁም ኢትዮጵያ ለምታስተናግዳቸው ለ1ሚሊየን ስደተኞች አገልግሎት የሚውል ነው፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ የረድኤት ኤጀንሲዎች የአሜሪካን እህል ማከፋፈላቸውን እንዲቀጥሉ ዩኤስኤይድን ፈቃድ ማግኝት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ነገር ግን ትራምፕ ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ሰራተኞች ከስራቸው ማስናበታቸውን ተከትሎ ይህን ፈቃድ የሚያስፈጽም አካል አልተገኘም ፡፡
በዚህ ምክንያት ከአሜሪካ በምታቀርበው እህል ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች ድጋፍ የሚያደርጉት በትግራይ የሚገኙ የእርዳታ ድርጅቶች ጥምረት ስርጭቱን ለማቆም ተገዷል፡፡
ጥምረቱ ከዚህ ቀደም በመጋዘኖች ውስጥ የሚገኙ የምግብ ክምችቶችን ለማከፋፈል ደግሞ ለነዳጅ፣ ለጭነት መኪና እና ለአሽከርካሪዎች የሚከፍለው ገንዘብ እንደሌለው አሶሼትድ ፕረስ በዘባው ጠቅሷል።
ከዚህ ውስጥ 300 ሺ ሰዎችን ለአንድ ወር መመገብ የሚችል 5 ሺህ ሜትሪክ ቶን በአንድ መጋዘን ውስጥ የሚገኝ ሲሆን እህሉ ለተረጂዎች ሳይደርስ ሊበላሽ እንደሚችል ዘገባው የአካባቢውን የእርዳታ አስተባባሪዎች ጠቅሶ አስነብቧል፡፡
ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉም የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ፣ በሽታ እና ሞትን ሊያስከትል እንደሚችል ተነግሯል፡፡
የክልሉ የጤና ስርአት በተገቢው ልክ አላገገመም ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች አሁንም እንደተዘጉ ናቸው ፣ በ2024 የህጻናት የተመጣጠነ ምግብ ዕጥረት 21 በመቶ ደርሶ ነበር፡፡
አሁን፣ የተመጣጠነ ምግብን ለማሻሻል የሚረዱ ብዙ መርሃ ግብሮች ቆመዋል ይላሉ የእርዳታ ሰራተኞች።
አክለውም መድኃኒቶችንና ክትባቶችን ለማዳረስ የሚደረጉ ፕሮጀክቶች መቆማቸውን እና በደርዘን የሚቆጠሩ የተፈናቀሉ ሰዎች ካምፖች የውሃ ምንጮች መቋረጣቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህ የተነሳም የዩኤስኤይድን ክፍተት ሊሞላ ባይችል እንኳን መሰረታዊ የምግብ እና የመድሀኒት ስርጭቶችን ሊያግዝ የሚችል ድጋፍ በቅርቡ ካልተደረገ ከፍተኛ ጉዳት ሊመዘገብ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡