ሱዳናዊያን ተቃዋሚዎች ለሁለተኛ ቀን የሀገሪቱን ዋና ዋና መንገዶችን ዘጉ
ሱዳናዊያን መንገዶችን የዘጉት “ክብራችን ይመለስ” በሚል ወታደራዊ መንግስትን በመቃወም ነው
በሱዳን የአንድ ዳቦ ዋጋ ወደ 50 የሱዳን ፓውንድ ማደጉ ነዋሪዎችን አስቆጥቷል
ሱዳናዊያን ተቃዋሚዎች ለሁተኛ ጊዜ የሀገሪቱን ዋና ዋና መንገዶችን ዘጉ።
በሱዳን ባሳለፍነው ጥቅምት በአብደላ ሀምዶክ (ዶ/ር) በሚመራው የሲቪል አስተዳድር ላይ የሀገሪቱ ጦር መፈንቅለ መንግስት መፈጸሙን ተከትሎ ሱዳናዊያን ለተቃውሞ ወደ አደባባይ ወጥተዋል።
ይህ በዚህ እንዳለም ሩሲያ እና ዩክሬን ወደ ጦርነት መግባታቸውን ተከትሎ የዓለም ነዳጅ እና ስንዴ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት በሱዳን የዳቦ ዋጋ ከ35 ፓውንድ ወደ 50 ፓውንድ ሊያሻቅብ ችሏል።
“ክብራችን ይመለስ” በሚል መፈክር ወደ አደባባይ ለተቃውሞ የወጡት ሱዳናዊያን ዛሬም ለሁለተኛ ጊዜ የአገሪቱን ዋና ዋና መንገዶች መዝጋታቸውን ካርቱም የሚገኘው አል ዐይን ዘጋ አሳውቆናል።
ተቃዋሚዎቹ አልሲተን፣ ኦማክና አል-ማሽታል፣ የመሳሰሉ ዋና ዋና የካርቱም መንገዶች መዝጋታቸውንም ነው የተገለጸው።
“ወታደራዊ አገዛዝ ያብቃ፣ የዳቦ የዋጋ ጭማሪ ተቀባይነት የለውም እና ክብራችን ይመለስ” ቀደም ካሉ ወራት አንስቶ እስከ ዛሬዋ እለት በሚልየን የሚቆጠሩ ሱዳናውያን በሀገሪቱ ከተሞች ላይ ባደረጓቸው ተቃውሞዎች ሲያንጸባርቋቸው የተሰሙ ጥያቄ አዘል መፈክሮች ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጀነራል አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ወታደራዊ መንግስት ጥያቄዎችን ከማስተናገድና የህዝቡን የልብ ትርታ ከማድመጥ ይልቅ በሰልፈኞች ላይ የወሰደውና ያልተመጣጠነ ነው የተባለለት የኃይል እርምጃም በበርካታ ሱዳናውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗልም ተብሏል።
የሰብዓዊ መብቶች እስከመጣስ በደረሰው የመንግስት እርምጃ የተቆጡ ሱዳናውያን፤ ከትናንት ጀምሮ ካርቱምን ጨምሮ በተለያዩ ሀገሪቱ ከተሞች ላይ የ”ክብራችን ይመለስ” ተቃውሞ በማሳማት ላይ ናቸው።
በመምህራን ማህበር እና ተቃውሞ በሚመራው ኮሚቴ እንደተጠራ በሚነገርለት በዚህ ሰልፍ፤ ባለፈው ሳምንት በደቡብ ዳርፉሯ ኒያላ ከተማ የተካሄደ ሰልፍን ተከትሎ ፖሊስ በንጹሃን ሰልፈኞች እና መምህራን ላይ የወሰደውን ያልተመጣጠነ እርምጃ ለማውገዝ የተደረገ ሰልፍ እንደነበርም ተገልጿል።
ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው ከሆነ ትናንት በኦምዱርማን ግዘት ውስጥ በተካሄደው ሰልፍ ባቢከር አል-ራሺድ የተባለ ሰልፈኛ ከጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ተመቶ ሞቷል።
ባቢከር፤ የወርሃ ታህሳሱን ተቃውሞ ሲመራ በተመሳሳይ መንገድ የተገደለውን ባዳዊ አል-ራሺድ ወንድም መሆኑን ያስታወሰው የኮሚቴው መግለጫ፤ “ባቢከር አል-ራሺድ በሱዳናውያን ዘንዳ መቼም የማይዘነጋ ሰማዕት ነው” ሲልም ገልጾታል።
በትናትናው የተቃውሞ ሰልፍ በተለይም በካርቱም፣ ኦምዱርማን፣ ሴናር፣ማዳኒ፣ገደራፍ እና ባህሪ ከተሞች፤ የሱዳን ፖሊስ በሰልፈኞች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ አስለቃሽ ጋዝ ሲጠቀም እንደነበር የአይን እማኞች አል-ዐይን ተናግሯል።
በጀነራል አልቡርሃን የሚመራው ወታዳራዊ መንግስት እንደፈረንጆቹ ጥቅምት 25 መፈንቅለ መንግስት በማካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክን እና ካቢኔያቸውን ከስልጣን በማስወገድ በትረ ስለጣኑን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠረ ወዲህ፤ ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ሱዳን በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች።
የፖለቲካ ቀውሱን ተከትሎ እየተስተዋለ ያለው የኢኮኖሚ ቀውስም ሀገሪቱ ወደማያባራ ሁከት ውስጥ እንዳይከታት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስጋት ከሆነ ሰነባብቷል።
በዚህም አላቆመም፤ አሜሪካን ጨምሮ የአልቡርሃን ጆሮ ያላገኙ ሀገራት እና ተቋማት በሱዳን ላይ የተላያዩ ማዕቀቦች በመጣል ላይ ናቸው።
በያዝነው ሳምንትም አሜሪካ በሱዳን ተጠባባቂ ኃይል ላይ ማዕቀብ መጣሏ የሚታወስ ነው።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ዋቢ በማድረግ በድረ-ገጽ ላይ እንዳመላከተው ከሆነ፤ በተጠባባቂው የፖሊስ ኃይል ላይ ማዕቀብ ሊጣል የቻለው በሱዳን የተፈጠረውን አመጽ ተከትሎ “በወሰደው ያልተመጣጠነ እርምጃ እና በፈጸመው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ነው” መሆኑን አስታውቋል።