ምርጫው በአንድ የግል እጩ በቀረበው ቅሬታ መሰረት ከሰኔ 14 ተራዝሞ ነው ዛሬ በመካሄድ ላይ ያለው
በኦሮሚያ ነገሌ ምርጫ ክልል ምርጫ እየተካሄደ ነው።
ምርጫው ለሕዝብ ተወካዮች እና ለክልል ምክር ቤቶች የሚወዳደሩ ዕጩዎች የሚወዳደሩ ሲሆን ዛሬ ጠዋት 12 ሰዓት ተጀምሯል።
የነገሌ ምርጫ ክልል ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ አማኑኤል ብርሃኑ ከ150 በላይ ታዛቢዎችና የምርጫ አስፈጻሚዎች መመደባቸውን ገልጸዋል፡፡
ዛሬ ጠዋት በተጀመረው የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ የኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነትን ለመከላከል ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በነገሌ ምርጫ ክልል ለሁለቱም ምክር ቤቶች ሁለት በግል፣ አንድ ከኢዜማ እንዲሁም አራት ከብልጽግና ፓርቲ ዕጩዎች ለውድድር መቅረባቸው ተመላክቷል፡፡
ዛሬ በመካሄድ ላይ ያለው ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ሊካሄድ የነበረ ነው፡፡
ሆኖም ምርጫው አንድ የግል እጩ ተወዳዳሪ ባቀረቡት ቅሬታ በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ትዕዛዝ ተቋርጦ ዛሬ እንዲካሄድ ተወስኖ ነበር፡፡
በውሳኔው መሰረትም እየተካሄደ ይገኛል እንደ ምርጫ ክልሉ ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ አማኑኤል ብርሃኑ ገለጻ፡፡
በምርጫ ክልሉ ስር ከሚገኙ 139 ምርጫ ጣቢያዎች መካከል ድምጽ ያልተሰጠባቸው 30 የምርጫ ጣቢያዎች ቦርዱ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ድምጽ እንዲሰጥ በወሰነው መሰረት እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡