የዓለም ባንክ ለአፍሪካ የምግብ ዋስትና ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ አጸደቀ
ባንኩ ለምግብ ዋስትና ድጋፍ ያደረገው በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት አፍሪካ ተጎጂ ሆናለች በሚል ነው
ኢትዮጵያ እና ማዳጋስካር የምግብ ደህንነት ችግር ያለባቸው ሀገራት ናቸው ተብሏል
የዓለም ባንክ አፍሪካ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የምግብ እና ነዳጅ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ የበለጠ ተጎጂ ናት በሚል የ2 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ አጽድቋል።
እንደ ሲጂቲኤን ዘገባ በምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ያሉ ሀገራት በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ለምግብ ዋስትና ችግር የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።
ይሄን ተከትሎም ከዚህ በፊት ከሩሲያ እና ዩክሬን በሚገዙት ስንዴ ጥገኛ የነበሩ የአፍሪካ ሀገራት ወደ ከፋ የምግብ ዋስትና ችግር እንዳይገቡ በሚል ባንኩ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
በሁለቱ የአፍሪካ ቀጣናዎች ካሉ ህዝቦች መካከል 66 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ሲሆን ድጋፉ በሀምሌ ወር ውስጥ ካልደረሳቸው የሚራቡ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ባንኩ ገልጿል።
በምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ያሉ ሀገራት በተደጋጋሚ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአንበጣ መንጋ፣ ግጭቶች እና ሌሎች ጉዳቶችን ማስተናገዳቸው የምግብ ደህንነታቸው አደጋ ውስጥ የገቡ ዜጎች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።
ከ4 ወራት በፊት የተጀመረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ደግሞ በአፍሪካ የምግብ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎችን ቁጥር ከፍ አድርጓል።
የዓለም ባንክ፤ በኢትዮጵያ 22 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች፣ በማዳጋስካር ደግሞ 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች የምግብ ደህንነት ችግር እንዳለባቸው በመጠቆም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብሏል በመግለጫው።