የተመድ የጸጥታው ም/ቤት ቋሚና ተለዋጭ አባላት በኢትዮጵያ ጉዳይ ምን አሉ?
የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ በአብዛኛው የምክርቤቱ አባላት ድጋፍ አግኝቷል
በተመድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ከም/ቤቱ ስለትግራይ በተነሱ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል
የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚና ተለዋጭ አባላት ትናንት ምሽት በትግራይ ክልል ጉዳይ ተሰብስበው ነበር፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ስላለው ቀውስ ስብሰባ ያደረጉት አምስቱ ቋሚ አባላት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይና ብሪታኒያ ሲሆኑ 10 ተለዋጭ አባላት ደግሞ እስቶኒያ፣ ሕንድ፣ አየርላንድ፣ ኬንያ፣ሜክሲኮ፣ ኒጀር፣ ኖረዌይ፣ ሴንት ቬንሰንትና ገሬናዲንሰ፣ቱኒዚያና ቬትናም ናቸው፡፡
በተመድ የቻይና አምባሳደር፤ ሀገራቸው በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ እየተከታተለች መሆኑን ገልጸው የጸጥታው ም/ቤት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማክበር እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ ቤጅንግ አሁን ላይ ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጎን መሆኗንም አስታውቃለች፡፡
በዚህ ስብሰባ ላይ በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር፤ በትግራይ ክልል ያለው ግጭት እንዲቆም መደረግ እንዳለበት ገልጸው፤ ያልተገደበ የሰብዓዊ ተደራሽነት ሊኖር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ የአሜሪካ ተወካይ በግጭቱ ተጠያቂነትም እንዲሰፍን የጠየቁ ሲሆን ፤ ያለገደብ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ክልሉ የማይሄድ ከሆነ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ሊሞቱ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
የምክርቤቱ ተለዋጭ አባል የሆነችው ኬንያ በበኩሏ አሁን ላይ በትግራይ ያለውን ሁኔታ በሚመለከት ከሃሰተኛ መረጃዎች መጠበቅ እንደሚገባ ገልጻ ሰብዓዊ እርዳታዎች እንዲጠናከሩ ጠይቃለች፡፡ መንግስት ከሰሞኑ የወሰደው የተኩስ አቁም እርምጃ የሚደነቅ መሆኑንም ጎረቤት ኬንያ አስውቃለች፡፡
ሁሉም አካላት የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት እና ሉዓላዊነትን መቀበልና ማክበር እንደሚገባቸውም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኬንያ አምባሳደር አስታውቀዋል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያውን ሁኔታ በትክክል መረዳት እንደሚገባም አቋሟ መሆኑን ናይሮቢ ገልጻለች፡፡ ኢትዮጵያ የቀደመ ስልጣኔ ያላት ሀገር ናት ያለችው ኬንያ አሁን ላይ ከኢትዮጵያ ሕዝብና ከመንግስት ጋር መቆም እንደሚገባ ገልጻለች፡፡
በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል የሆነችው ሩሲያ፤ ጉዳዩ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መሆኑን በድጋሚ አስታውቃለች፡፡ ሞስኮ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ያወጀው የተናጠል ተኩስ አቁም ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን አስታውቃለች፡፡ ሕንድ በበኩሏ ለኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነትና ሉዓላዊነት መከበር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጻለች፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ የማይካድራ ጭፍጨፋ፣ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ከመኖሪያ ቀዬው ላለፉት ዓመታት መፈናቀላቸው ተገቢ የህግ አግባብ ተሰጥቶት መዘጋት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
"ኢትዮጵያውያን ለጊዜው ድሆች ብንሆንም ተስፋና ጥበብ ያለን ሕዝብ ነን" ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ ይህ ስብሰባ ራሱ የተደረገው የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጅ ካወጀ በኋላ መሆኑ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡
የባለፈው ወር የምክርቤቱ ሰብሳቢና ተለዋጭ አባል የሆነችው እስቶኒያ የኢትዮጵያ መንግስት ያወጀው የተናጠል የተኩስ አቁም በፈጎ እርምጃ በመሆኑ በደስታ እንደምትቀበለው አስታውቃለች፡፡ ከዚህ ባለፈም በትግራይ ሁሉም ግጭት እንዲቆም ጥሪ ያቀረበች ሲሆን ገደብ የሌለበት ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጻለች፡፡ የመብራት፣ የስልክና ሌሎች አገልግሎቶች ወደነበሩበት መመለስ እንዳለባቸውም ነው እስቶኒያ የገለጸቻ፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ሮዝመሪ ዲካርሎ፤ የሕወሃት ሃይሎች እስካሁን ተኩስ እንዳላቆሙ ገልጸዋል፡፡ በመቀሌ ከተማ የመብራትና የኢንተርኔት አገልግሎት እንደሌለ ያነሱት ምክትል ዋና ጸሐፊዋ፤ ዋና ዋና የሚባሉ መሰረተ ልማቶችም መውደማቸውን አንስተዋል፡፡ ሁሉም ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያደርጉ ሰራተኞች መተላለፊያዎችን ክፍትና ሰላማዊነት እንዲያረጋግጡም የመንግስታቱ ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ሮዝመሪ ዲካርሎጠይቀዋል፡፡ እስቶኒያ የተኩ አቁሙ በጣም ተገቢ ነው፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ የማይካድራ ጭፍጨፋ፣ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ከመኖሪያ ቀዬው ላለፉት ዓመታት መፈናቀላቸው ተገቢ የህግ አግባብ ተሰጥቶት መዘጋት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ "ኢትዮጵያውያን ለጊዜው ድሆች ብንሆንም ተስፋና ጥበብ ያለን ሕዝብ ነን" ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ ይህ ስብሰባ ራሱ የተደረገው የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጅ ካወጀ በኋላ መሆኑ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም ምክትላቸው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ትናንት መቀመጫቸውን አዲአ በባ ላደረጉ የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ አባላት ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ በማብራሪያቸውም መንግስት ሰብዓዊ ድጋፍን ለማጠናከር እንደሚሰራ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መንግስት የትግራይን ቀውስ በውይይት ለመፍታት ማቀዱንና አዲስ መንግስት ከተመሰረተ በኋላ ሁሉን አቀፍ ወይይት እንደሚደረግም ለዲፕሎማቶቹ ገልጸዋል፡፡