ወልዲያ ዩኒቨርስቲ ምን ተዘጋጅቶ ነው ተማሪዎች የጠራው?
ዩኒቨርስቲው የአንደኛ ዓመት ተማሪዎችን ነው በመቀበል ላይ ያለው
“ለመማር ማስተማር የሚሆኑ መሰረታዊ ቁሶችን አሟልተናል”- የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት
ከህወሓት ጋር በመካሄድ ላይ ባለው ጦርነት ምክንያት ለከባድ ዘረፋ እና ውድመት የተዳረገው ወልዲያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹን እየተቀበለ ነው፡፡
ዩኒቨርስቲው መጋቢት 5 እና 6 ቀን 2014 ዓ.ም በቅጥር ግቢው እንዲገኙ የጠራቸውን የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎቹን ነው እየተቀበለ ያለው፡፡ ከጠዋት ጀምሮም ትራንስፖርት በማመቻቸት ተማሪዎቹን በመቀበል ላይ ይገኛል፡፡
ጥሪውን ተቀብለው ወልዲያ ከተማ የደረሱ በርካታ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲው እየገቡ መሆኑንም የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አበበ ግርማ ለአል ዐይን አማርኛ በስልክ ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርስቲው ለከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ መዳረጉን ተከትሎ ምን ይዞ እና ምን ዝግጅት አድርጎ ተማሪዎችን እንደጠራ የጠየቅናቸው ፕሬዝዳንቱ ለመማር ማስተማር የሚሆኑ መሰረታዊ ግብዓቶችን አሟልተናል ይላሉ፡፡
የምግብ፣ የመኝታ እና ሌሎችም ለመማር ማስተማር ሂደቱ መሰረታዊ የሆኑ ግብዓቶች መሟላታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
ዩነቨርስቲው ነገና ከነገ ወዲያ ሃሙስ ደግሞ በቅጣት ሊመዘግብ የጠራቸው የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎቹ በቁጥር 3 ሺ900 ያህል ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ 3 ሺ ያህሉ በጥሪው መሰረት ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዶ/ር አበበ ነግረውናል፡፡
ከህወሓት ጋር በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት አዋሳኝ በሆኑ የአማራ ክልል አካባቢዎች አሁንም እንደቀጠለ ነውና ምን ዋስትና ኖሮ ተማሪዎቹ እንደተጠሩ የጠየቅናቸው ፕሬዝዳንቱ አሁን ላይ ከስጋት የጸዳ ሰላማዊ ሁኔታና እንቅስቃሴ በወልዲያ ከተማና በአካባቢው እንዳለ ነግረውናል፡፡
የሚያጋጥም ምንም ነገር እንዳይኖር እቅድ ተዘጋጅቶ ከጸጥታ አካላት ጋር በጋራ እየሰራን ነው የሚሉት ዶ/ር አበበ ስጋቱ በውጭ እንደሚወራው አይደለም ሲሉም ነው የሚናገሩት፡፡
የተማሪዎቹ ምዝገባ ሲጠናቀቅ በመጪው ሃሙስ ከከተማው ማህበረሰብ ጋር የአብሮነትና የጋራ እራት መርሃ ግብር እንደሚኖርም አክለዋል፡፡
ቀስ በቀስ ተማሪዎቹን የበለጠ የሚያረጋጉና ስነ ልቦናዊ ይዞታቸውን ከፍ የሚያደርጉ ሙያዊ ስራዎች እንደሚሰሩም ገልጸዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ዩኒቨርስቲው ከጦርነቱ በፊት በተለያዩ የስልጠናና የትምህርት መስኮች 12 ሺ ገደማ ተማሪዎችን ያስተምር ነበር፡፡
ሆኖም አሁን በቢሊዮን ብሮች ለሚገመት የንብረት ውድመት ተዳርጓል፡፡ ይህን ተከትሎም ቀደም ሲል ሲያስተምራቸው የነበሩ ነባር ተማሪዎቹን ለመቀበል አልቻለም፡፡ በሌሎች ዩኒቨርስቲው ተመድበው እንዲማሩ በመደረግም ላይ ይገኛል እንደ ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር አበበ ገለጻ፡፡
በቀጣዩ የትምህርት ዓመት ግን ዩኒቨርስቲው ነባር ተማሪዎቹን መልሶ ይጠራል፡፡ ለዚህም ዩኒቨርስቲውን በግብዓቶች መልሶ ለማደራጀት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
ሆኖም ተመራቂ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች እስከ መጪው ወርሃ ሰኔ ይጠራሉ፡፡ ለዚህም ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል፤ ዶ/ር አበበ፡፡
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ ከሆነ ዩኒቨርስቲው 900 ገደማ ተመራቂ ተማሪዎች አሉት፡፡
ዘለግ ላሉ ወራት በህወሓት ተዋጊዎች እጅ ሆና የቆየችው የሰሜን ወሎ ዞን ርዕሰ ከተማ ወልዲያ ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ነጻ መውጣቷ ይታወሳል፡፡