መንግስት “አያሌ በደሎች ሲፈጸምባቸው” ነበር ያላቸውን ወልዲያ እና ሌሎች ከተሞችን ነጻ ማውጣቱን አስታወቀ
በአሁን ሰአት ሰቆጣ አካባቢ ውጊያ መኖሩን ሚኒስትሩ ገልጸዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጦርነቱን መንግስት ማሸነፉ ስማይቀር የህወሓት ታጣቂዎች እጃቸውን እንዲሰጡ በቅርቡ ጥሪ አቅርበው ነበር
የኢትዮጵያ መንግስት “ረዘም ላለ ጊዜ በጠላት እጅ የቆዩና አያሌ በደሎች ሲፈጸምባቸው” ነበር ያላቸውን የሰሜን ወሎ ዞን ዋና ከተማ ወልዲያንና ሌሎች የዞኑ ከተሞችን ነጻ ማውጣቱን አስታውቋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ የአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የመከላከያ ሰራዊት፣ በአማራና አፋር የጸጥታ ሃይሎች ባደረጉት ዘመቻ የሰሜን ወሎ ዞንን ሙሉ በሙሉ ከህወሓት ነጻ መውጣቱን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ“ሌሊቱን በሙሉና ዛሬ ረፋዱን ጀግኖቹ የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራና የአፋር የጸጥታ ኃይሎች ከንሥሮቹ የአየር ኃይል ጋር ባደረጉት የተቀናጀ የማጥቃት ዘመቻ የሳንቃን፣ የሲሪንቃን፣ የሰሜን ወሎ ዋና ከተማ የሆነችውን ወልድያ ከተማን፣ ሐራን፣ ጎብየን፣ ሮቢትን እና ቆቦን፣ ሙሉ በሙሉ” መቆጣጠራቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለያዪ ግንባሮች በመንግስት ጦር እየተመታ ያለው የህወሓት ኃይል ወደ ኮረም እና አላማጣ አቅጣጫ ማምራቱን የመንግስት ጦር እግርበእግር እየተከታተለው ነው ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
በአሁን ሰአት ሰቆጣ አካባቢ ውጊያ መኖሩን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በፌደራል መንግስትና በህወሃት ሃይሎች መካከል ያለው አለመግባባት ወደ ወታደራዊ ግጭት ከገባ ከ8 ወራት በኋላ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፤ጦሩን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱ ይታወሳል፡፡
ነገርግን በኢትዮጵያ መንግስት በሽብር የተፈረጀው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች ጥቃት መክፈቱንና ይህንም ለመቀልበስ እንደሚንቀሳቀስ መንግስት መግለጹ ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በቅርቡ ከግንባር ሆነው ባስተላለፉት መልእክት፤ ጦርነቱን መንግስት ማሸነፉ የማይቀር ስለሆነ የህወሓት ታጣቂዎች እጃቸውን ለጸጥታ አካላት እንዲሰጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዘመቱ በኋላ በአማራ ክልል በህወሓት ተይዘው የነበሩ ደሴና ከምቦልቻ ከተሞችን ጨምሮ በርካታ ትንንሽ ከተሞችን ነጻ ማውጣታቸው ይታወሳል፡፡