አሜሪካ የሃውሲ አማጽያንን “በአሸባሪነት” ልትፈርጅ ነው ተባለ
ፕሬዝዳንት ባይደን አማጽያኑን በሽብርተኝነት ስለመፈረጅ እያጤኑ መሆናቸውን ቀደም ሲል መግለጻቸው አይዘነጋም
የአሜሪካው የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ለመመክር ስብሰባ መቀመጡ ነው የተገለጸው
አሜሪካ የሃውሲ አማጽያንን በድጋሚ በአሸባሪነት ልትፈርጅ መሆኗ ተገለጸ፡፡
የአሜሪካው አግሺዮስ ድረ-ገጽ( axios website) ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው “በኋይት ሀውስ የሚገኘው የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት የሃውሲ ሚሊሻዎችን በአሸባሪነት ለመፈረጅ የሚያስችለውን እርምጃ ለመውሰድ ተቃርቧል” ብሏል።
“የየመን አማጽያኑን በሽብርተኝነት ለመፈረጅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር የኢንተር ኤጀንሲ ስብሰባ አድርጓል” ሲልም አክሏል ድረ-ገጹ ባወጣው መረጃ።
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በሃውሲ መሪዎች ወይም የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚፈጽሙ አካላት ላይ ማዕቀብ ሊጥል እና በሽብርተኝነት ሊፈርጅ እንደሚችል ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ወር ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡
“አዎ፤ ጉዳዩን በማጤን ላይ ነን” ሲሉም ነበር የተደመጡት ባይደን የስልጣን ዘመናቸውን አንደኛ ዓመት አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፡፡
በየመን ያለውን ጦርነት ለማቆም የጦርነቱን ተሳታፊ አካላትን ጭምር የሚመለከት በመሆኑ ቀላል እንደማይሆንም ነበር ባይደን የተናገሩት፡፡
አሜሪካ ከአሁን ቀደም በፕሬዝዳንት ትራምፕ የአስተዳደር ዘመን አመጽያኑን በሽብርተኝነት ፈርጃ ነበር፡፡ ሆኖም አዲሱ የባይደን አስተዳደር ውሳኔውን ቀልብሶ ፍረጃውን አንስቷል፡፡
የሃውሲ አማጽያን ባለፈው ወር ንጹሃን ዜጎችንና መገለወገያዎችን ዒላማ ያደረገ ጥቃትን በአቡ ዳቢ መፈጸማቸው ይታወሳል፡፡
በጥቃቱ ሁለት ህንዳውያን እና አንድ ፓኪስታናዊ በድምሩ ሶስት ንጹሃን ተገድለዋል፡፡
ይህን ተከትሎም የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድርጊቱን በጽኑ እንዲያወግዝና እርምጃ እንዲወስድ ጠይቃ ነበረ፡፡
በአሜሪካ የዩኤኢ አምባሳደር ዩሱፍ አል ኦታይባም የባይደን አስተዳደር በንጹሃን ላይ እንዲህ ዐይነት አረመኔያዊ ድርጊት የፈጸመውን ቡድን በድጋሚ በሽብርተኝነት እንዲፈርጅ መጠየቃቸውም የሚታወስ ነው፡፡
የአቡ ዳቢ ልዑል አልጋ ወራሽ እና የዩኤኢ ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድም ከአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሊሎድ ኦስቲን ጋር የአማጽያኑን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል “ቆራጥ ዓለም አቀፋዊ አቋም” መያዝ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመከሩትም ባለፈው ወር ነበር፡፡