የኳታሩ አለም ዋንጫ በየመን የጫት ዋጋን አንሯል
የመናውያን በኤደን፣ ሰንአ እና ሌሎች ከተሞች የእግርኳስ ግጥሚያዎች ለማየት መሰባሰባቸው የጫት ፍላጎቱን በእጥፍ ጨምሮታል
ጦርነት ባደቀቃት ሀገር በየቀኑ ከ20 ሚሊየን ዶላር በላይ በጫት ንግድ ይንቀሳቀሳል
የመናውያን እግር ኳስን እንደሚወዱ ይነገርላቸዋል።
ኳታር ያሰናዳችውን የአለም ዋንጫንም ሰብሰብ ብለው ማየት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
ጦርነት ክፉኛ በጎዳት ሀገር በየጎዳናውና አደባባዩ ግዙፍ ስክሪኖች ተተክለው ጨዋታውን እየተመለከቱ ነው።
ይህ መሰባሰባቸውም የጫት ፍላጎታቸውን ጨምሮት የዋጋ መናርን አስከትሏል ነው የተባለው።
በተለይም በኤደን እና ሰንአ የጫት ፍላጎቱ በእጥፍ መጨመሩ ተዘግቧል።
ጫት በአለም ጤና ድርጅት በአደንዛዥ እፅነት ቢመዘገብም በየመን ከልጅ እስከ አዋቂው አዘውትሮ ይወሰዳል።
አብዛኞቹ የመናውያን ከስአት በኋላ የጫት ቅጠልን የመብላት አልያም የተፈጨ ጫት የመጠጣት ልማድ እንዳላቸው ነው የሚነገረው።
እናም የአለም ዋንጫ በኳታር ሲጀመር (ረጅም ስአታትን ተቀምጦ ለመከታተል ሲባል) ይሄው የጫት ፍላጎት መናሩ ነው የተገለፀው።
ይህም መሰል አጋጣሚዎችን ለሚጠቀሙ ነጋዴዎችም ገበያው ደርቶላቸዋል ነው የተባለው።
የጫት ዋጋ ከአለም ዋንጫው በፊት ከነበረበት እጅግ የተጋነነ ጭማሪ ማሳየቱን ተጠቃሚዎቹ ይገልፃሉ።
የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከገባች ስምንት አመት በሆናት የመን፥ ጫት የበርካታ ዜጎቿን ማህበራዊ ስሪት አፈራርሶ ከባድ ኪሳራ ውስጥ ጥሏቸዋል።
በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብትም ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ እያደረሰ መሆኑን የመንግስታቱ ድርጅት ገልጿል።
የመናውያን ግን እንደ ጫት ንግድ አዋጪ የለም እያሉ ጫት መትከሉንም ሆነ መቃሙን ገፍተውበታል።
በየቀኑ ከ20 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚንቀሳቀሰው በዚሁ ቅጠል መሆኑንም መከራከሪያ ያደርጉታል።
ከማንኛውም አዝርዕት በአራት እጥፍ የሚልቅ ገቢን ከጫት ንግድ እንደሚገኝም ጥናቶች ያመላክታሉ።
ይሁን እንጂ ከጦርነት የተረፈው የየመን ትውልድ በጫት ሱስ ህይወቱ በአጭሩ የመቀጨት እድሉ ሰፊ ነው።