የዓለም የሬዲዮ ቀን መቼና እንዴት መከበር ጀመረ?
በዓለም ዙሪያ ከ44 ሺህ በላይ ሬዲዮ ጣቢያዎች በየእለቱ መረጃዎችን ለዓለም ህዝብ ያደርሳሉ
ከ5 በሊየን በላይ የሚሆኑ የዓለማችን ህዝቦች የሬዲዮ አድማጮች መሆናቸውንም መረጃዎች ይጠቁማሉ
ሬዲዮ በጣም ተዓማኒ የመረጃ ምንጭ ከሆኑት ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ሲሆን፤ ለዓለማችን ህዝቦች ዋነኛ የመረጃ ምንጭ ከሆኑት ውስጥ አሁንም ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደተሰለፈ ቀጥሏል።
ምንም እንኳ የኢንተርኔቱ ዓለም በመደበኛ የመገናኛ ብዙሃን ዘዴዎች ላይ የራሱ የሆነ ጫና ቢያሳድርም ራዲዮ ግን አሁንም ኃያልነቱን እና ጉልበተኝነቱን አላጣም።
በዛሬው እለትም የዓለም የሬዲዮ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ13ኛ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ5ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው።
ዓለም አቀፍ የራዲዮ ቀን እንዴት መከበር ጀመረ?
ዓለም አቀፍ የራዲዮ ቀን ዘንድሮ “ሬድዮ፡የክፍለ ዘመን መረጃ ሰጪ፣ አዝናኝና አስተማሪ ” በሚል መሪ ሃሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ13ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ5ኛ ጊዜ በመከበር ላይ ይገኛል።
የዓለም ራዲዮ ቀን እንዲከበር በስፔን የራዲዮ አካዳሚ አነሳሽነት ጥያቄው በፈረንጆቹ በ2010 ለዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (UNESCO) የስራ አመራር ከቀረበ በኋላ የተባበሩት መንግስታት ጉዳዩን ተቀብሎ ዓለም አቀፍ የራዲ ቀን በየዓመቱ የካቲት 5 እንዲከበር ወስኗል።
በመሆኑም የመጀመሪያው የራዲዮ ቀን በፈረንቹ የካቲት 5/2011 የተከበረ ሲሆን ዛሬ ለ13ኛ ጊዜ “ሬድዮ፡የክፍለ ዘመን መረጃ ሰጪ፣ አዝናኝና አስተማሪ” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው።
ሬዲዮ በዓለም አቀፍ ደረጃ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከዓመታት በፊት ባጣው መረጃ መሰረት በዓለም ዙሪያ ከ44 ሺህ በላይ የራዲዮ ጣያዎች እንዳሉ ጠቁሟል።
በኢነዚህ የራዲዮ ጣቢያዎች አማካኝነትም በዓለም ዙሪያ ያሉ ከ5 ቢሊየን በላይ ሰዎች ማለትም ከዓለም ህዝብ ከ70 በመቶ በላይ በየእለቱ ከራዲዮን እንደሚያዳምጡም ነው መረጃው የሚጠቅመው።
ከ100 ዓመታት በላይ የመደመጥ ታሪክ ያለው ራዲዮ ሰዎች በየእለቱ በስራ ቦታቸው፣ በትራንፖርት ላይ እንዲሁም በመኖሪያ ቤታቸው ሆነው ያደምጡታል።
ይህም ራዲዮ በዚህ የኢንተርኔት ዘመንም ኃያልነቱን ሳያጣ እንንቆይ ካደረጉት ውሰጥ አንዱ እንደሆነ ይነገራል።
ሬዲዮ በኢትዮጵያ
ሬዲዮና ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ጥብቅ ቁርኝት አላቸው። ያኔ ቴክኖሎጂው ባልደረሰብት እና እንዲህ እንደ አሁኑ መረጃ እንደልብ በማይገኝበት ጊዜ ሬዲዮ ብዙ ሰርቷል።
የያኔው የኢትዮጵያ ሬዲዮ የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ብሄራዊ ሬዲዮ ቀዳሚውን ሚና ተጫውቷል።ሬዲዮን በማስተዋወቅም ረገድ ፈር ቀዳጅ ነው።
በቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ “መልካም ፈቃድ” በ1920ዎቹ መጨረሻ ስራ የጀመረው የኢትዮጵያ ሬዲዮ መረጃ በቀላሉ ሊገኝ በማይችልበት በዛን ጊዜ ብቸኛ አማራጭ ሆኖ አገልግሏል።
ላለፉት 88 ገደማ ዓመታትም የብዙሃኑን ኢትዮጵያዊ ቀልብ ለመግዛት፤ ከብዙሃኑም ልብ ውስጥ ለመቀመጥ የቻሉ ስራዎችን እየሰራም ከዛሬ ደጃፍ ደርሷል።
የኢትዮጵያ ሬዲዮን ፈለግ በመከተልም ብዙ የሬዲዮ ጣቢያዎችም ተመስርተዋል። አሁን ላይ ከ60 በላይ የተለያዩ ቋንቋዎች በአጭር፣መካከለኛ እና ረጅም እንዲሁም በኤፍ.ኤም ሞገዶች የሚያሰራጩ ከ75 በላይ የራዲዮ ጣቢያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በኢትዮጵያ ያለው የሬዲዮ ቁጥር ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ እየተበራከተ መጥቷል። በአሁኑ ሰዓት በሃገሪቱ በተለይም በከተሞች ከሚገኙ የራዲዮ ጣቢያዎች መካከልም አብዛኞቹ የኤፍ.ኤም ጣቢያዎች ናቸው። የመጀመሪያው ኤፍ.ኤም የሬዲዮ ጣቢያ ኤፍ.ኤም 97.1 ነው። የመጀመሪያው የግል የሬዲዮ ጣቢያ ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 ነው።
ከ2003 ዓ/ም ጀምሮ ራሱን በኮርፖሬትነት በአዲስ መልክ ያደራጀው ሬዲዮ ፋናም ከኤፍ.ኤም 98.1 በተጨማሪ በርካታ ኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ያሉት ቀዳሚ የሃገሪቱ የሚዲያ ተቋም ነው።