ሃውቲዎች በሰንአ የሚገኘውን የተመድ የሰብአዊ መብቶች ጽህፈትቤት ተቆጣጠሩ
በዋና ጽህፈት ቤቱ ውስጥ የሚገኙ ንብረቶችና ሰነዶችን መዝረፉንም ነው የመንግስታቱ ድርጅት ያስታወቀው
የየመኑ ቡድን በሰኔ ወር በተመድ መስሪያ ቤቶችና በአለማቀፍ ግብረሰናይ ተቋማት የሚሰሩ 60 ሰዎችን ማሰሩ ይታወሳል
የሃውቲ ታጣቂ ቡድን በሰንአ የሚገኘውን የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ጽህፈት ቤት መውረሩ ተነገረ።
ቡድኑ በጽህፈት ቤቱ የነበሩ ተሽከርካሪዎች፣ ልዩ ልዩ ንብረቶችና ሰነዶችን መዝረፉንም ነው የተመድ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ የገለጹት።
“ሃውቲዎች በፍጥነት ጽህፈት ቤቱን ለቀው መውጣት አለባቸው፤ የወሰዱትን ሁሉንም ንብረትና ሰነድም ሊመልሱ ይገባል” ብለዋል ከፍተኛ ኮሚሽነሩ።
አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው የሃውቲዎችን ምላሽ ለማካተት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካ ገልጿል።
የተመድ የሰብአዊ መብቶች ጽህፈት ቤት በሰንአ የሚገኘውን ዋና ቢሮውን እንዲሁም በሃውቲዎች ቁጥጥር ስር ያሉ ቢሮዎቹን የዘጋው በሰኔ ወር 2024 ነበር። ይሁን እንጂ አለማቀፍ እውቅና ያለው የየመን መንግስት በተቆጣጠረው አካባቢ ስራውን መቀጠሉን ይገልጻል።
ሃውቲዎች በሰኔ ወር በተመድ መስሪያ ቤቶችና በአለማቀፍ ግብረሰናይ ተቋማት የሚሰሩ 60 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለው ማሰራቸው ይታወሳል።
ከእነዚህ ውስጥም ስድስቱ የተመድ የሰብአዊ መብቶች ጽህፈት ቤት ሰራተኞች ናቸው ተብሏል።
የየመኑ ቡድን 60 የመንግስታቱ ድርጅት ተቋማት እና የግብረሰናይ ድርጅቶች ሰራተኞችን በቁጥጥር ስር ባዋለ ማግስት “የአሜሪካ - እስራኤል የስለላ መረብ” አባላት ናቸው ያላቸውን አካላት መያዙን መግለዙም አይዘነጋም።
ቡድኑ በለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስልም 10 የመናውያን በሀገሪቱ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ተመልምለው የስለላ ስራ ሲሰሩ እንደነበር ሲናገሩ ይደመጣሉ።
የመንግስታቱ ድርጅት ግን ሰራተኞቹ በግዳጅ ሃውቲዎች የሚፈልጉትን እንዲሉ ተደርገዋል በሚል የቀረበውን ቪዲዮ አጣጥሎታል።
ሰንአን ጨምሮ አብዛኛውን የየመን ክፍል የተቆጣጠሩት ሃውቲዎች በአለማቀፍ ደረጃ እውቅና ከተሰጠውና ሳኡዲ መራሹ ጥምረት ከሚያግዘው የየመን መንግስት ጋር ከ2014 ጀምሮ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መግባቱ ይታወቃል።
በኢራን እንደሚደገፍ የሚነገርለት ቡድን እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከጀመረች ወዲህ ለሃማስ አጋርነቱን ማሳየቱ የሚታወስ ሲሆን፥ ቴል አቪቭን እያገዙ ነው ባላቸው ሀገራትና አለማቀፍ ተቋማት ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ ይገኛል።