የዩክሬን ፕሬዝደንት “ፑቲን በቡድን 20 ጉባዔ የሚገኝ ከሆነ ላይ አልሳተፍም” አሉ
የቡድን 20 ጉባዔ በመጪው ህዳር 15 እና 16 በኢንዶኔዥያ የሚካሄድ ይሆናል
ምዕራባውያን፤ ሞስኮ በኪቭ ላይ በፈጸመችው ወረራ በቡድን 20 ጉባዔ ላይ የመቀመጥ ሞራል የላትም እያሉ ነው
የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ “ፐሬዝዳንት ፑቲን በቡድን 20 ጉባዔ የሚገኝ ከሆነ ላይ አልሳተፍም” ማለታቸው ተሰምቷል።
ዩክሬን የቡድን-20 አባል ባትሆንም የሀገሪቱ መሪ ፕሬዝደንት ቮሊድሚ ዘለንስኪ በጉባዔው ላይ እንዲሳተፉ ግብዣ ቀርቦላቸዋል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በፈረንጆቹ በህዳር 15 እና 16 በኢንዶኔዥያ በሚካሄደው የቡድን- 20 ጉባዔ ላይ ለመገኘት የሚያስችላቸው ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል።
እንደ ኤኤፍፒ ዘገባ ከሆነ ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ "የሩሲያ ፐሬዝዳንት ፑቲን በጉባዔው ላይ ከተገኙ ዩክሬን አትሳተፍም " ብለዋል።
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ፤ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የጀመረችን ወታደረዊ ዘመቻ ምክንያት ከቡድን-20 እንድትባረር ደጋግመው ሲጠይቁ መቆየተቻው አይዘነጋም።
ብሪታኒያን ጨምሮ በርካታ የምዕራባውያን ሀገራትም እንዲሁ ሞስኮ በኪቭ ላይ በፈጸመችው ወረራ በቡድን-20 ጉባዔ ላይ የመቀመጥ “የሞራል መብት” የላትም ሲሉ ተደምጠዋል።
በተቃራኒው የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሊን ፑቲን በጉባዔው ቢገኙ መልካም ነው ብለዋል።
የኢንዶኔዥያው ፕሬዝዳንት ጆኮ ዊዶዶ የሩሲያው አቻቸው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጉባዔው እንዲሳተፉ መጋበዛቸውን አስታውቀዋል።
ከዩክሬን ጋር ተያይዞ ለሚነሳው ጉዳይም ፤ ጉባዔው ሀገራቱ ተቀራርበው እንዲነጋገሩ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑ አነስተዋል ፕሬዝዳንቱ ጉባዔውን በማስመልከት ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ።
ፑቲን በጥቅምት ወር መገባደጃ ላይ በኢንዶኔዥያ ባሊ በሚካሄደው የቡድን-20 ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ አልወሰንኩም ማለታቸው ይታወሳል።
ቭላድሚር ፑቲን በቅርቡ በካዛክስታን የተካሄደውን ስብሰባ ተከትሎ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "ወደዚያ የመጓዜ ነገር ገና አልተወሰንም፤ ነገር ግን ሩሲያ በእርግጠኝነት ትሳተፋለች፤ እያሰብንበት ነው" ሲሉም ተናግረዋል።