የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት ማካተቱን እንደሚቀጥል ተገልጿል
የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉአላዊነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ዋና ኃላፊ ሆነው መሾማቸውን የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ፡፡
ለ13 ዓመታት የአረና ሊቀመንበር ሆነው የቆዩት አቶ አብርሃ በዶ/ር ሙሉ ነጋ በሚመራው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ነው በኃላፊነት የተመደቡት፡፡ የብልጽግና ፓርቲ አቶ አብርሃን “ለነፃነት የታገለ ወጣት ሲሆን በርካታ ጊዜያትንም በእስር አሳልፏል” ሲል ገልጿቸዋል፡፡
አቶ አብርሃ ደስታ በመቐለ ዩንቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር የነበሩ ሲሆን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ አስተያየት በመስጠት ይታወቃል፡፡
በተመሳሳይ ዜና አቶ አታክልቲ ኃይለስላሴ የከተማዋ ከተማ ከንቲባ በመሆን መሾማቸው የሚታወስ ሲሆን የከተማዋን ነዋሪዎች የልማትና የጸጥታ ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገልጸዋል፡፡
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) በትግራይ እየተዋቀረ ያለው ጊዜያዊ የመንግስት አስተዳደር ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ኣካቶ እንደሚመሰረት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በዚህም መሰረት አረና፣ ትዴፓ እና አሲምባን የመሳሰሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት በክልሉ ካቢኔ ውስጥ እንዲገቡ እየተደረገ ሲሆን ከዚህ በፊት በነበረው የክልሉ ነበራዊ ሁኔታ እነዚህ አካላት በፖለቲካ አመለካከታቸው የተነሳ ሲታሰሩ፣ ሲገደሉና ሲሳደዱ ስለመቆየታቸው ተገልጿል፡፡
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከሰኞ ታህሣሥ 5 ቀን 2013 ዓ/ም ጀምሮ ወደ ስራ የገባ ሲሆን ትናንት ማክሰኞ ዕለት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) በመቐለ ከተማ የመንግሥት ሰራተኞችን አወያይተዋል፡፡ በከተማዋ የመንግሥት ስራዎች በመጀመር ላይ ሲሆኑ ሁለት ክፍለ ከተሞች ሙሉ በሙሉ ስራ መጀመራቸውንም ዶ/ር ሙሉ ገልጸዋል፡፡