ፖለቲካ
የቀድሞው የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ፍርድ ቤት ቀረቡ
ከኦነግ ሸኔ ጋር በጋራ በመሆን የመንግስትን መረጃና ሚስጥሮች አሳልፈው ሲሰጡ እንደነበረም ተገልጿል
አምባሳደር አዲስ ዓለም ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገራት ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት ለማበላሸት ሲሰሩ ነበር ተብሏል
የቀድሞው የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር እና የሕወሓት ከፍተኛ አመራር የነበሩት አምባሳደር አዲስ ዓለም ባሌማ (ዶ/ር) ዛሬ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተገለጸ፡፡
አምባሳደር አዲስ ዓለም (ዶ/ር) ኢትዮጵያን ወክለው አምባሳደር በነበሩበት ዘመን ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገራት ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት ለማበላሸት እና ለማስቆም ተፅዕኖ ሲፈጥሩና ሲሰሩ እንደነበር መርማሪ ፖሊስ ለችሎት አስረድቷል፡፡ የቀድሞው ከፍተኛ አመራር የመንግስትን መረጃና ሚስጥሮች አሳልፈው ሲሰጡ እንደነበርም መርማሪው ገልጿል፡፡
ከኦነግ ሸኔ ከፍተኛ አመራሮች ጋር መረጃ ሲለዋወጡ እና የመንግስትን ምስጢር አሳልፈው በመስጠት ለተፈጸሙ ወንጀሎች በጋራ ሲሰሩ እንደነበርም ተገልጿል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡ በሕግ ሲፈለጉ ከነበሩት የሕወሓት ቡድን አባላት መካከል አንዱ የሆኑት አዲስ ዓለም ባሌማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከትላንት በስቲያ መግለጻቸው ይታወሳል።