በትግራይ ክልል የጦር መሳሪያ የታጠቀ ሁሉ እስከ ማክሰኞ ድረስ ትጥቅ እንዲያስረክብ ጥሪ ቀረበ
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቤኔ ከነገ ጀምሮ ወደ ስራ እንደሚገባ ተገልጿል
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቤኔ ከነገ ጀምሮ ወደ ስራ እንደሚገባ ተገልጿል
በህጋዊም ሆነ በህገ ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ የታጠቀ ማንኛውም ግለሰብ እስከማክሰኞ ታህሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ትጥቁን በአቅራቢያው ለሚገኝ የጸጥታ አካል እንዲያስረክብ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) አሳስበዋል።
“ከማክሰኞ በኋላ የቤት ለቤት ፍተሻ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ በፍተሻው ትጥቅ የተገኘበት ግለሰብ ተጠያቂ ይሆናል” ብለዋል።
በትግራይ ክልል ሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የንግድ ድርጅቶች አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንመር ገልጸዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ የክልሉን ካቤኔ ማዋቀሩን የገለጹት ዶክተር ሙሉ ፣ ካቤኔው ከነገ ጀምሮ ወደ ስራ እንደሚገባ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል።
የመንግስት ሰራተኞችም ከፊታችን ሰኞ ጀምረው ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ አሳስበው በተጠቀሰው ቀን ወደ ስራ ገበታው የማይመለስ የመንግስት ሰራተኛ ካለ በገዛ ፈቃዱ ስራውን እንደለቀቀ ተደርጎ እንደሚወሰድም ገልጸዋል።
መቀሌን ጨምሮ አብዛኛው የክልሉ ከተሞች ላይ ሰላምና መራጋጋት መፈጠሩን ጠቁመው፤ “የንግድ ድርጅቶች ከነገ ጀምሮ ወደ መደበኛ ስራቸው መመለስ አለባቸው” ብለዋል።
ይህን በማያደርጉ የንግድ ድርጅቶች ላይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እርመጃ መውሰድ እንደሚጀምርም አመልክተዋል።
የክልሉ ነዋሪዎች ለጊዜያዊ አስተዳዳሩ የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።