ህወሓት ከአፋር ክልል መሬት “ወጥቻለሁ” ማለቱን የአፍር ክልል“ውሸት ነው” አለ
አለምአቀፉ ማህበረሰብ “በአሸባሪው ህወሀት” የሚነሱ ፕሮፓጋንዳዎችን አይስማ ብሏል
ህወሓት ከተቆጣጠራቸው የአፋር ክልል ወረዳዎች “ሙሉ በሙሉ ወጥቻለሁ” ማለቱ ውሸት ነው ሲል የአፋር ክልል ገለጸ
የህወሓት ሃይሎች ከጎረቤት አፋር ክልል ሙሉ በሙሉ መውጣታቸውን ሮይተርስ የህወሓትን ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳን ጠቅሶ ከሁለት ቀናት በፊት መዘገቡ ይታወሳል፡፡
አቶ ጌታቸው ከአፋር ክልል መውጣት ማለት በጣም አስፈላጊ የሆኑ የምግብ እርዳታ በርሃብ ውስጥ ላለችው ትግራይ ይደርሳል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
ነገርግን የአፋር ክልል መንግስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች ከያዟቸው የአፋር ክልል ቦታዎች አለመውጣታቸውን አስታውቋል፡፡
“አሸባሪው ህወሀት በከባድ መሳሪያ በመታገዝ ከወረራቸው በአፋር ክልል የኪልበቲ ረሱ ዞን ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ ወጥቻለሁ በማለት ከሰሞኑ ከእውነት የራቀ የሀሰት የማደናገሪያ ፕሮፖጋንዳ በማሰራጨት ላይ ይገኛል።” ብሏል የክልሉ መንግስት ባወጣው መግለጫ፡፡
የህወሓት ኃይሎች በተቆጣጠሯቸው በአፋር ክልል የኪልበቲ ረሱ ዞን ወረዳዎች በከባድ መሳሪያ በመታገዝ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት በመክፈት ከ500ሺህ በላይ ዜጎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል ያለው ክልሉ ህወሓት የውሸት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት የህዝብ ስቃይ እንዲራዘም እና ሰብአዊ እርዳታ በተፈለገው መልኩ እንዳይደርስ እያደረገ ነው ሲል ይከሳል፡፡
ህወሃት “እስካሁን ድረስ ከኪልበቲ ረሱ ወረዳዎች ከመጋሌ፤ ከበራህሌ፤ ከኮነባ፤ ከአብአላ ወረዳ፤ ከአብአላ ከተማ አስተዳድር አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ለቅቆ ያልወጣ እና የአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ የቡድኑ እንቅስቃሴ እንደቀጠለ ነው።” ብሏል ክልሉ፡፡
የክልሉ መንግስት እንዳለው ሰላምና መረጋጋት እንዲስፍን ከተፈለገበመደብደብ “የአፋርን ወሰን ጥሶ በመግባት ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ ያደረሰው አሸባሪው ቡድን አካባቢውን በሙሉ ለቅቆ መውጣት ይገባል፡፡”
አለምአቀፉ ማህበረሰብ “በአሸባሪው ህወሀት” የሚነሱ ፕሮፓጋንዳዎች ወደ ጎን በመተው መሬት ላይ ያለውን ሀቅ እንዲረዳ የክልሉ መንግስት ጥሪ አቅርቧል፡፡