የተኩስ አቁሙን ፍሬያማነት ለማረጋገጥ የሚቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁም ብሏል ህወሓት
የትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ፍላጎቶች የሚያሟሉ እርዳታዎችን በተገቢ ሁኔታና ወቅት የሚያገኝ ከሆነ በመንግስት የተደረገውን ተኩስ አቁም ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አስታወቀ፡፡
ህወሓት የተኩስ አቁሙን ፍሬያማነት ለማረጋገጥ የሚቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ ሲል አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ መንግስት ትናንት አደረግሁ ያለውን ተኩስ አቁም የተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው የትግራይ ህዝብና መንግስት ጦርነቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ግልጽ ያለ አቋም አላቸው ያለው ህወሓት ገና ከመነሻው ፖለቲካዊ ችግሮች ሁሉ በሰላማዊ መንገዶች እልባት ሊያገኙ እንደሚገባ አድርገን ነበር ይላል፤ ለስኬቱ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጉን በመጠቆም፡፡
ያለፉትን 4 ዓመታት ይህንኑ ስናደርግ ነበር የሚልም ሲሆን ከ17 ወራት በፊት ሁሉም የሰላም አማራጮች በመዘጋታቸው ህልውናን ለማረጋገጥ በሚል ተገዶ ወደ ጦርነት መግባቱን ያትታል በመግለጫው፡፡
ሁሌም ምርጫው ከጦርነት ይልቅ ሰላም እንደሆነ በመግለጽም አሁን እንኳን ሳይቀር ጦርነት ምርጫው እንዳልሆነ ያስቀምጣል፡፡
የትግራይ ህዝብ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰብዓዊ እርዳታ ቢደረግለትም እርዳታዎቹ ወደ ክልሉ እንዲገቡ ይፈቀድ እንዳልነበርም ነው መግለጫው የሚያትተው፡፡
መንግስት የተቋረጡ የስልክ እና የባንክ አገልግሎቶችን መልሶ ቢሆን እንኳን የብዙዎችን ህይወት ለመታደግ ይቻል እንደነበርም ይጠቁማል፡፡
ከጦርነት በኋላ ህይወት በትግራይ ምን ይመስላል?
ህወሓት አሁንም ቢሆን የትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ እርዳታዎችን እንዲያገኝ ሁኔታዎች በጊዜው ከተመቻቹ ተኩስ አቁሙን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሆነ ገልጿል፡፡
የተኩስ አቁሙን ፍሬያማነት ለማረጋገጥ የሚቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ ሲልም ነው ያስታወቀው፡፡
መንግስት ለትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ እርዳታዎች ሳይቆራረጡ እንዲደርሱት ቃል ከመግባት የዘለለ ተግባርን እንዲፈጽምም ጥሪ አቅርቧል፡፡
ሆኖም ይህ በእንዲህ እንዳለ ፖለቲካዊ እና ሰብዓዊ ሁኔታዎችን ማያያዝ ተቀባይነት የለውም ያለም ሲሆን የትግራይ ህዝብና መንግስት ለሰላም እድል ለመስጠት የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ አስታውቋል፡፡
መንግስት ትናንት ሰብአዊ እርዳታዎች ሳይቆራረጡ እንዲደርሱ በማሰብ ግጭት ለማቆም መወሰኑን አስታውቋል፡፡
እርምጃው የተመድ የሰብዓዊ እርዳታ የአየር በረራዎች ቁጥር እንዲጨምር እንዲሁም ለእርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ነዳጅና ጥሬ ገንዘብ የሚቀርብበትን ስርዓት የተሳለጠ እንዲሆን በማሰብ የተወሰደ መሆኑንም ማስታወቁ ይታወሳል። መንግስት በክልሉ ሰብዓዊ እርዳታዎችን እያቀረበ መሆኑን ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
ህወሓት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት መፈረጁም አይዘነጋም፡፡