የሁለቱ ሱዳናዊያን የጦር ጀነራሎች ወዳጅነት እና ጠላትነት እስከ ምን?
ጀነራል አልቡርሀንና ጀነራል ሄመቲ አምባገነኑን የፕሬዝዳንት አልበሽር አገዛዝን በጋራ ጥለዋል
ሁለቱ የጦር መሪዎች ትናት ወደ ጦርነት ከማምራታቸው በፊት የቅርብ ወዳጆች እንደነበሩ ይነገራል
የሱዳን ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች የሆኑት ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሀን እና ሌተናንት ጀነራል ሙሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ከሚመሩትን ጦር ይዘው ወደ ውጊያ አምርተዋል።
ትናንት የተጀመረው ይህ ጦርነት ንጹሀንን ጨምሮ ወታደራዊ እና ሌሎች ጉዳቶችን እስከትሏል ተብሏል።
እነዚህ የሱዳን ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ማን ናቸው? ከዚህ በፊት የነበረው ወታደራዊ ህይወታቸውስ ምን ይመስላል?
በፈረንጆቹ 1960 በሰሜናዊ ሱዳን ኩንዱ የተወለዱት ጀነራል አልቡርሀን ከወጣትነታቸው ጀምሮ እስካሁን ድረስ ሀገራቸው በወታደርነት እያገለገሉ ናቸው።
ወታደራዊ ትምህርቶችንን በሱዳን፣ ግብጽ እና ጆርዳን የተከታተሉት ጀነራል አልቡርሀን የሱዳን መከላከያ ዋና አዛዥ ከመሆናቸው በፊት የምድር ጦር ወዛዥ፣ የሀገር ዳር ድንበር ጦር አዛዥ እና በሌሎችም ወታደራዊ ሀላፊነት አገልግለዋል።
የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሀሰን አልበሽር ከስልጣን መነሳት ተከትሎ ወደ ሀገር መሪነት ብቅ ያሉት አልቡርሀን በቻይና እና በሌሎች ሀገራትም የሱዳን ወታደራዊ አታቼ ሆነው አገልግለዋል።
በዳርፉር ግዛት የተወለዱት ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ወይም ሄመድቲ ወደ ውትድርናው ዓለም ከመቀላቀላቸው በፊት ግመልን በመጠቀም ወደ ሊቢያ፣ ቻድ እና ማሊ ወርቅ እና ሌሎች ማዕድናትን በመነገድ ይታወቃሉ።
በዳርፉር ያሉ የወርቅ ማውጫ ስፍራዎችን መቆጣጠራቸውን እና ተጽዕኗቸው ምክንያት በቀድሞው ፕሬዝዳንት አልበሽር ትኩረትን እንዳገኙ ይነገራል።
በፕሬዝዳንት አልበሽር ወታደራዊ ሹመት ተሰጥቷቸው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦርን እንዲመሩም ከ10 ዓመት በፊት ሀላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
የሄመቲ ወደ ወታደራዊ አመራር መምጣትን የሱዳን ወታደራዊ አመራሮች በወቅቱ ተቃውመው ነበርም ተብሏል።
አሁን ላይ ከ100 ሺህ በላይ ወታደሮች የሚመሩት ጀነራል ሄመቲ በጀነራል አልቡርሀን በሚመራው መከላከያ ሰራዊት ጋር ይፋዊ ጦርነት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ጀነራል ዳጋሎ በ2019 ፕሬዝዳንት አልበሽር በሀይል ከስልጣን እንዲነሱ ትልቁን ግፊት ሰርተዋል በሚል በሱዳናዊያን እንደሚወደዱም ይገለጻል።