ሁሉም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ለትግራይ ክልል የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ሊያደርጉ ነው
የክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ድጋፍ በቀጣዮቹ ቀናት ወደ ትግራይ ክልል እንደሚደርሱ ተገልጿል
ሁሉም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ለትግራይ ክልል የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ሊያደርጉ ነው
ዛሬ በበይነ መረብ በተካሔደ ስብሰባ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የክልል ፕሬዚደንቶች እና የከተማ ርዕሰ መስተዳድሮች ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳድር እንዲሁም ለክልሉ ሕዝብ የሚሆን የአንድነት ንቅናቄን አስጀምረዋል።
የአንድነት ንቅናቄው ክልሎች፣ የፌደራል ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመከናወን ላይ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደግፉ ለማስቻል ያለመ ነው።
በጊዜያዊ አስተዳደሩ አማካኝነት ለትግራይ ሕዝብ ከሚደርሱ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶች በተጨማሪ፣ የክልልፕሬዝደንቶች አስተዳደሩ የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ግዴታዎቹን ለመወጣት እንዲችል ቀጥተኛ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
በዚህም መሠረት፣ እያንዳንዱ ክልል ቃል የገባቸው ተሽከርካሪዎች፣ ልዩ ልዩ ቁሳቁስ እና መገልገያዎች፣ ለአርሶ አደሮች የሚቀርቡ ዘሮች፣ አምቡላንሶች፣ መድሃኒት እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ በሚቀጥሉት ቀናት ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ይደርሳሉ ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግራይን መልሶ ለመገንባቱ የአንድነት ንቅናቄ የሚችሉትን አስተዋጽኦ ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል ሲል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ገልጿል።
ከውይይቱ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት “የትግራይ ክልል ተመልሳ በምትገነባበት በዚህ ወቅት በሀገራዊ አንድነት ድጋፍ ለማሰባሰብ ተስማምተናል” ብለዋል። አክለውም “ለዚሁ የአንድነት ተግባር የአንድ ወር ደሞዜን፣ ከመደመር መጽሐፍ ሽያጭ 200 ሺህ ብር እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በኩል ሦስት የውኃ ማመላለሻ ባለታንከር መኪናዎችን አዋጥቻለሁ” ካሉ በኋላ ሁሉም ሰው ትግራይን መልሶ በመገንባቱ የአንድነት ንቅናቄ እንዲሳተፍ ጥሪዬን አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በሕወሓት ኃይል መካከል በትግራይ ክልል የተካሔደው ውጊያ ክልሉን ለከፍተኛ ቀውስ ዳርጓል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ለክልሉ ህዝብና መንግስት የምግብ እና መሰል አቅርቦቶችን በማድረስ ላይ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት በማሳወቅ ላይ ነው፡፡ ይህን የተገነዘቡ የተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን በመሆን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
ድጋፍ ለሚፈልገው የትግራይ ክልል ህዝብ በበቂ መጠን ድጋፎች እንዲቀርቡ የሰብዓዊ ድርጅቶች ያለምንም ገደብ ወደ ክልሉ እንዲገቡ በመንግስት ላይ ጫናዎች ሲደረጉ እንደነበረም የሚታወስ ነው፡፡ ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች ሙሉ ፈቃድ ሳይሰጥ የቆየው የኢትዮጵያ መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገደቡን በማላላት በአሁኑ ወቅት በትንሹ 26 ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶች ወደ ክልሉ በስፋት ገብተው እንዲሰሩ አድርጓል፡፡