የአማራ ብልጽግና ፓርቲ በብድር ስም ገንዘብ የወሰዱ አመራሮቹን ከኃላፊነት አነሳ
ፓርቲ ከተቀማጭ ገንዘቡ ለአመራሮችና ሰራተኞች ሲሰጥ የነበረው የረጅም ጊዜ ብድር አሰራር ከህገ ደንቡ የሚጣረስ መሆኑን አስታውቋል
ፓርቲው አመራሮቹ ከዛሬ ጀምሮ ከያዙት የመንግስትና የፓርቲ ኃላፊነት እንዲነሱ መደርጉን አስታውቋል
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ በብድር ስም ገንዘብ የወሰዱ አመራሮቹን ከኃላፊነት አነሳ፡፡
ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመዋዋል ከተቀማጭ ገንዘቡ ለአመራርና ሰራተኞቹ የረጅም ጊዜ ብድር የመስጠት አሰራር ስርዓት እንደነበረ ያስታወቀው ፓርቲው አሰራሩ ከህገ ደንቡ የሚቃረን ሆኖ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
በመሆኑም በብድር ስም የወጣው የፓርቲው ገንዘብ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከነ ወለዱ ታስቦ ተመላሽ እንዲደረግና ዝርዝር ሁኔታው ተጣርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ በብድር ስም ገንዘብ የወሰዱ አመራርና ሰራተኞችም ከያዙት የመንግስትና የፓርቲ ኃላፊነት ከዛሬ የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እንዲነሱ መደረጉን ከደቂቃዎች በፊት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ለአሰራሩ ተገዥ በመሆን ተፈፃሚ የማያደርጉ ግለሰቦች ካጋጠሙ በህጉ መሰረት ተጠያቂነታቸው የሚከናወን ይሆናልም ነው ፓርቲው በመግለጫው ያለው፡፡
ፓርቲው የውሳኔውን ዝርዝር ሁኔታ በውስጥ አሰራሩ መሰረት ለመላ አመራሮቹና አባላቱ በተዋረድ በግልጽ ይፋ እንደሚደረግም አስታውቋል፡፡
የመሪው ብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ጸጋ አራጌ የፓርቲው ሃብትና ንብረት ለከፍተኛ ምዝበራ እየተጋለጠ ነው በሚል ጻፉት የተባለ የአቤቱታ ደብዳቤ ሲያነጋግር ነበረ፡፡
ብልጽግና በወቅቱ ጉባዔ አለማካሄዱን በማስታወቅ በፓርቲው ውስጥ ተስተውሏል ያሉት የህግ ጥሰትና የአሰራር መዛነፍ እንዲስተካከል የጠየቁት አቶ ጸጋ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት አመራሮች 60 ሚሊዮን ብር ተከፋፍለው መውሰዳቸውንና ከ100 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ የፓርቲው ገንዘብ ለብክነት መዳረጉን በደብዳቤው መጠቆማቸው ሲገለጽም ነበረ፡፡
ለዚህ ምላሽ የሚመስልን መግለጫ ያወጣው የአማራ ብልጽግናም የተባለው ምዝበራ ፍፁም መሰረተ ቢስ ውንጀላ መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡
የፓርቲው ጽ/ቤት “በፓርቲው ወጪ የተደረገ ምንም አይነት ገንዘብ የለም፤ ይህንንም በፓርቲው በውስጥና በውጭ ኦዲተር ኦዲት የተደረገበትን ማስረጃ ማንኛውም አካል በማንኛውም ጊዜ ቀርቦ መጠየቅና ማረጋገጥ የሚችለው እውነታ ነው” ሲልም ነበር መግለጫ ያወጣው፡፡
ሆኖም ዛሬ ባወጣው መግለጫ በብድር ስም ገንዘብ በወሰዱ አመራሮቹና ሰራተኞቹ ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡