የባሊስቲክ ሚሳኤል ጥቃቱ የተሰነዘረው በየመን በሚንቀሳቀሱት የሀውሲ አማጽያን ታጣቂዎች ነው
ዪኤኢ የተቃጣባትን የባሊስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ማምከኗን ገለጸች፡፡
የተባበሩት አረብ ኢምሬት በሀውሲ ታጣቂዎች የተቃጣባትን የባሊስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ማክሸፏን የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ታጣቂዎቹ የሚሳኤል ጥቃቱን ሊያደርሱ የነበረው በአገሪቱ መዲና አቡዳቢ ከተማ ሲሆን የአገሪቱ ጦር አደጋውን እንደቀለበሰ የአገሪቱ ዜና አገልግሎት (ዋም) ዘግቧል፡፡
የሀውሲ ታጣቂዎች ሁለት የባሊስቲክ ሚሳኤሎችን ለዛሬ ለእለተ ሰኞ እ.ኤ.አ ጥር 24 አጥቢያ እሁድ ሌሊቱን ወደ አቡዳቢ ያስነወጨፉ ሲሆን ሚሳኤሎቹ አደጋ ሳያደርሱ እንዲመክኑ ተደርገዋል ተብሏል፡፡
በቀጣይ በአገሪቱ ደህንነት ላይ የሚደረጉ ማናቸውንም ጥቃቶች እንደሚመክት የገለጸው የዩኤኢ መከላከያ ሚኒስቴር በቀጣይ እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡
በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ መናኸሪያ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ዩኤኢ በሚሳኤል ጥቃቱ የአውሮፕላን በረራዎች ላይ ያደረሰው ተጽዕኖ እንደሌለም ተገልጿል፡፡
የሀውሲ ታጣቂዎች የባሊስቲክ ሚሳኤሉን ወደ አቡዳቢ ያስወነጨፉት የዓረብ ሊግ ታጣቂዎቹ በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ከጠየቁ ከደቂቃዎች በኋላ ነው፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ሰኞ በአቡዳቢ በፈጸሙት ተመሳሳይ ጥቃት የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉ እና ስድስት ገደማ ሰዎች መጎዳታቸው ይታወሳል፡፡
ይህንኑ ተከትሎ በፕሬዝዳንት ባይደን የሚመራው የአሜሪካ አስተዳደርም ታጣቂዎቹን በሽብርተኝነት ለመፈረጅ እያሰበበት መሆኑን መግለጹ አይዘነጋም፡፡