አውስትራሊያ የዓለም ቁጥር አንዱ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ኖቫክ ጆኮቪች ወደ ሃገሯ እንዳይገባ አገደች
ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሪሰን ማንም ከህግ በላይ አይደለም ሲሉ ጽፈዋል
ጆኮቪች ወደ አውስትራሊያ እንዳይገባ የታገደው የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን አልወሰደም በሚል ነው
አውስትራሊያ የዓለም ቁጥር አንዱ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ኖቫክ ጆኮቪች ወደ ሃገሯ እንዳይገባ አገደች፡፡
የአውስትራሊያ ኦፕን የሜዳ ቴኒስ ሻምፒዮና የ9 ጊዜ አሸናፊው ጆኮቪች የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን አልወሰደም መባሉን ተከትሎ ነው ወደ ሃገሪቱ እንዳይገባ የታገደው፡፡
ክትባቶችን እንደማይደግፍ ያስታወቀው ጆኮቪች ማንም አስገድዶ ሊከትበኝ አይችልም ሲል ከአሁን ቀደም ተናግሯል፡፡
በዚህም ክትባትን አስገዳጅ ያደረገችው አውስትራሊያ ወደ ሃገሯ እንዳይገባ ከልክላዋለች፡፡ መከተቡን የሚያሳይ ማስረጃ አላቀረበም በሚልም ቪዛውን መሰረዟም ነው የተነገረው፡፡
የቻይና እና የአሜሪካ ስፖርተኞች በአንድ ወገን ሆነው ሊጫወቱ ነው
ጆኮቪች ይህን ሳይጠየቅ ወደ ሃገሪቱ ሊገባ የሚችልበትን ፈቃድ ከዘንድሮ የውድድሩ አዘጋጆች አግኝቶ ነበር፡፡ ሆኖም ፈቃዱ ከሃገሪቱ የኮሮና ቫይረስ የቁጥጥር ህግ እና አሰራር ውጭ የተሰጠ ነው ያሉ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ለጆኮቪች ቪዛ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
ማንኛውም ወደ አውስትራሊያ የሚገባ ሰው ለሁለት ያህል ጊዜያት መከተብ አለበት፡፡ አለበለዚያ ተገቢውን የህክምና ፈቃድ ከሚመለከተው የሃገሪቱ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ማግኘት አለበት፡፡
የሜዳ ቴኒስ ኮኮቡ ጆኮቪች ግን ስለመከተቡም ሆነ ስለ ሌሎች የጤና ሁኔታዎች ያሳወቀው ነገር የለም፡፡ ከዚህ ነጻ ሊሆን የሚችልበትን ተገቢውን ፈቃድም አላገኘም ስለ ጉዳዩ መግለጫ እንደሰጡት እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ገለጻ፡፡
ይህን አሟልተው ለቀረቡ የውጭ ዜጎች ቪዛዎችን ሰጥተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ውጭ ግን “ማንም ሊገባ አይችልም፤ ማንም ከህግ በላይም አይደለም” ብለዋል፡፡
በሜልቦርን ተንገላቷል የተባለለት ጆኮቪች ዛሬ ሃሙስ ሃገሪቱን ለቆ እንዲወጣ እንደሚደረግም ነው የተገለጸው፡፡
በኢትዮጵያ እየተለመደ የመጣው ስኬትቦርዲንግ፤ እና የተጫዋቾቹ ፈተና
ይህ ከ11 ቀናት በኋላ በሚጀመረው ውድድር ተሳትፎ የሻምፒዮናነቱን ክብር ለመጠበቅ አያስችለውም፡፡ በዚህም ጠበቆቹ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንወስደዋለን ብለዋል፡፡
የሰርብ መንግስትም ጉዳዩን በቀላሉ የምመለከተው አይደለም የሁሉም ሰርቢያውያን ጉዳይ ነው ሲል አስታውቋል፤ ወደ ህግ እንደሚወስደው በማሳወቅ፡፡
ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ቩቺች በቤልግሬድ የአውስትራሊያ አምባሳደርን ጠርተው ማብራሪያ መጠየቃቸውና ጆኮቪች በውድድሩ እንዲሳተፍ ሊፈቀድለት እንደሚገባ መናገራቸውም ነው የተገለጸው፡፡