መንግሥት “ህወሓት የእርዳታ አውሮፕላኖች መቀሌ ኤርፖርት እንዳያርፉ ከልክሏል” ሲል ከሷል
ህወሓት የእርዳታ አውሮፕላኖች መቀሌ ከተማ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ እንዳያርፉ መከልከሉን የኢትዮጵያ መንግስት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በዚህ ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል ።
መንግስት በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች አስፈላጊው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
- “ከህወሓት ጋር ለመነጋገር የሚያስችል ኮሚቴ ተቋቁሟል” - ጠ/ሚ ዐቢይ
- አቶ ደመቀ ህወሓት ለጥፋት ዓላማ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ቁሳቁሶች እንዳያልፉ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳሰቡ
ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበርም አስፈላጊ መሰረታዊ ድጋፎች በየብስና በአየር ወደ ትግራይ ሲያጓጓዙ መቆየታቸውም ተገልጿል።
በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ይህንን የመንግስትን ጥረት "ጥላሸት ለመቀባትና የሃሰት ፕሮፖጋንዳውን ለመንዛት ሲል ወደ ክልሉ የሚገቡ ሰብአዊ ድጋፎች የሚገቡበትን ሂደት ለማስተጓጎል ሞክሯል" ሲል ነው መንግስት የገለጸው።
ህወሓት በየብስ የሚገቡትን ሰብዓዊ ድጋፎች ለትግራይ ህዝብ እንዳይደርሱ መንገድ በመዝጋትና የእርዳታ ማስተላልፊያ ኮሪደሮች አካባቢ ትንኮሳ በመፈጸም ሲያስተጓጉል ነበር ብሏል አገልግሎቱ።
ህወሓት ከራሱ "የፕሮፖጋንዳ ስሌት" ባሻገር ለትግራይ ህዝብ ግድ እንደሌለው በተግባር አሳይቷል” ሲልም መንግስት ቡድኑን ይከሳል።
መንግስት በቡድኑ በኩል የሚመጡ እንቅፋቶችን በመቋቋም አስፈላጊውን ያልተቋረጠ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ማድረጉ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ እውቅና የተሰጠው መሆኑንም ገልጿል።
መንግስት በየቀኑ መድሃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶች እንዲሁም የህጻናት አልሚ ምግቦች ወደ ክልሉ የሚላክበትን የአውሮፕላን በረራ ህወሓት ማስቆሙን አስታውቋል።
ከትናንት ጀምሮም ላልተወሰነ ጊዜ የእርዳታ አውሮፕላኖች መቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንዳያርፉ ህወሓት መከልከሉን የመንግስት ቃል አቀባይ ጽ/ቤት አስታውቋል።
መንግስት ይህ የህወሓት ቡድን እርምጃ ቡድኑ የትግራይን ህዝብ "የሃሰት ፕሮፖጋንዳው መሳሪያ ከማድረግ ውጪ ሌላ አላማ እንደሌለው ዳግም በተግባር የሚያረጋግጥ ነው" ብሏል።
ይህንን የህወሃትን ውሳኔ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያወግዘው የክልከላውንም ምክንያት እንዲያጣራም ጠይቋል።
በተጨማሪም መንግስት እስካሁን ሲያደርግ እንደቆየው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉ የትግራይ ክልል ዜጎች አስፈላጊው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል።