ፖሊስ፤ ፍርድ ቤቱ መስከረም አበራ በዋስትና እንድትፈታ በሰጠው ውሳኔ ላይ ይግባኝ ጠየቀ
ፍርድ ቤቱ፤ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ያስፈልገዋል በሚል በያየሰው ሽመልስ ላይ ተጨማሪ 7 የምርመራ ቀናትን ፈቅዷል
መስከረም አበራ በዋስ እንድትለቀቅ ፍርድ ቤቱ ወስኖ ነበር
ፖሊስ፤ ፍርድ ቤቱ መስከረም አበራ በዋስትና እንድትፈታ በሰጠው ውሳኔ ላይ ይግባኝ ጠየቀ፡፡
የተጠርጣሪዋን ጉዳይ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 6 ቀን 2014 ዓ/ም የተመለከተው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ነበር በ30 ሺ ብር ዋስትና ከእስር እንድትለቀቅ ያዘዘው፡፡
በተጠርጣሪዋ መኖሪያ ቤት 63 መጽሐፍትን እና 5 ሺ በሶፍት ኮፒ ያሉ መጽሐትን አግኝቻለሁ ያለው ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ያስፈልገኛል በሚል የተጨማሪ 14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡
ጥያቄው ውድቅ የተደረገበት ፖሊስ ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ መጠየቁንም የአል ዐይን ምንጮች አመልክተዋል፡፡
በምትሰጣቸው ጠንከር ያሉ አስተያየቶች እና ትችቶች የምትታወቀው መምህርት መስከረም አበራ “ኢትዮ ንቃት” የተሰኘ የዮቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት ናት፡፡
በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ የኢትዮ ፎረም የዮቲዩብ መገናኛ ብዙኃን አዘጋጅ የሆነውን የጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስን ጉዳይ ተመልክቷል፡፡
ከሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት አለው በሚል ጥርጣሬ በታሰረው በጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ባንክ አካውንት በአንድ ቀን 18 ሚሊዮን ብር እንደገባ እና 17 ሚሊዮኑ በዚያኑ ዕለት ወጪ እንደተደረገ ፖሊስ በችሎቱ አስረድቷል፡፡
በችሎቱ ያለ ጠበቃ የቀረበው ያየሰው በአዲስ አበባ ለ10 ያህል ዓመታት የኖርኩና ቋሚ አድራሻ ያለኝ በመሆኑ በዋስትና ልለቀቅ ይገባል በሚል ጠይቆ ነበር፡፡
ሆኖም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ያስፈልገዋል በሚል ተጨማሪ 7 የምርመራ ቀናትን ፈቅዷል፡፡
የተጠርጣሪው ጠበቃ ታደለ ገብረ መድህን ግን በውሳኔው ላይ ዛሬ ከሰዓት መልስ ይግባኝ ለመጠየቅ ስለመዘጋጀታቸው የአል ዐይን ምንጮች አመልክተዋል፡፡
ሌላኛው ፍርድ ቤቱ የተመለከተው ጉዳይ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አባል የሆነውን የቢኒያም ታደሰን ጉዳይ ነው።
ፖሊስ፤ ቢኒያም ስለ አዲስ አበባ እና ስለ ሌሎችም ጉዳዮች በፌስቡክ የማህበረሰብ ትስስር ገጽ ጽፏል ሲል አስረድቷል፡፡ "አዲስ አበባ የኢትዮጵያ እንጂ የኦሮሚያ ዋና ከተማ አይደለችም" ብሏል ሲልም ነው ፖሊስ ያቀረበው፡፡
ያመንኩበትን ነው የጻፍኩት ያለው ቢኒያምም "የታሰርኩት የተቃዋሚ ፓርቲ አባል በመሆኔ ነው" የሚል ምላሽን ሰጥቷል፡፡ በፌስቡክ ለጻፈው ተጠያቂው ራሱ መሆኑን በማገርም ፖሊስ አባሪዎቹን ለመያዝ ጊዜ ይሰጠኝ ማለቱን ተቃውሟል፡፡
ሆኖም ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ 7 የምርመራ ቀናትን ፈቅዷል።