“በውስጥ ጉዳያችን የትኛውንም ዓይነት ጣልቃገብነት እንቃወማለን”-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
“በሃገሪቱ መንግስት የድጋፍ ጥሪ እስከሚቀርብ ድረስ መጠበቅ የግድ ይላል”ም ነው ዐቢይ አህመድ ያሉት
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለዓለም አቀፍ ህግጋት ተገዥ እንዲሆንም ጠይቀዋል
“በውስጥ ጉዳያችን የትኛውንም ዓይነት ጣልቃገብነት እንቃወማለን”-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኩል የሚደረግ የትኛውንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጣልቃ ገብነትን የሚከለክሉ ዓለም አቀፍ ህግጋትን ተገዢነት በማስመልከት በጉዳዩ ላይ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያን የረጅም ዓመታት የሃገረ መንግስትነት እና የባለ ብዙ ወገን የትብብር ታሪክ በመግለጫቸው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ ጋባዥነት ብቻ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
“በሃገሪቱ መንግስት የድጋፍ ጥሪ እስከሚቀርብ ድረስ መጠበቅ የግድ ይላል”ም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ያሉት፡፡
ሃገራዊ ለውጡን በመቀልበስ “በህገ ወጥ መንገድ ወደ ስልጣን መመለስ በሚፈልገው ህወሓት አቀናባሪነት”በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ብሄርና ሃይማኖት ተኮር ጥቃቶች መፈጸማቸውንም ገልጸዋል፡፡
“ባሳለፍነው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ/ም ራሳቸው ‘መብረቃዊ’ ሲሉ የገለጹትን የክህደት ጥቃት ትግራይ በሚገኘው የሃገሪቱ ብሄራዊ ጦር ላይ ጨለማን ተገን አድርገው ፈጽመዋል”ያሉም ሲሆን በጦሩ ላይ የዝርፊያ ወንጀል መፈጸሙንም አብራርተዋል፡፡
ይህም በሃገሪቱ ህግ “የክህደትና የወንጀል ድርጊት ነው” እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፡፡
ይህ አልበቃ ብሎም በማይካድራ አምነስቲ እና ምናልባትም ‘ድርጊቱ በዓለም አቀፍ ወንጀል ሊያስጠይቅ የሚችል የጦር ወንጀል ነው’ሲል ያስታወቀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያረጋገጡት የንጹሃን ጭፍጨፋ ተፈጽሟል፡፡
ይህን ተከትሎም መንግስት ያወጣውን ህግ በግዛቱ የመተግበር ሙሉ መብት እንዳለው ማንኛውም ሉዓላዊ ሃገር “የሃገርን ሉዓላዊነት እና አንድነት የማስጠበቅ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል” ብለዋል፡፡
እርምጃው “ህግና ስርዓን የማስከበር እና ወንጀለኞችን ከህግ ፊት የማቅረብ ተልዕኮ ያለው ነው” ያሉም ሲሆን የዜጎችን ደህንነት እና አነስተኛ ጉዳት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ እንደሚፈጸም አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ብረት አንስቶ የፌዴሬሽኑን ህልውና አደጋ ላይ በጣለው አካል ላይ እየወሰድን ያለነው እርምጃ ዴሞክራሲን ከሚያበረታውና ኢ-ህገመንግስታዊ የመንግስት ለውጥን ከሚከለክለው የአፍሪካ የዴሞክራሲ ቻርተር ጋር ተጣጥሞ እንደሚፈጸምም እናምናለን” ብለዋል በመግለጫቸው፡፡
ኢትዮጵያ ጉዳዩን በራሷ ህግጋትና ዓለም አቀፍ ግዴታዎች መሰረት ለመፈጸም እንደምትችል ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁም ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የወዳጆቻችን ስጋት ቢገባንም በራሳችን የውስጥ ጉዳይ የትኛውንም ዓይነት ጣልቃገብነት እንቃወማለን” ሲሉም ጠንከር ያለ አቋምን በመግለጫቸው አንጸባርቀዋል፡፡
በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “ተቀባይነት ከሌለው እና ህገወጥ ከሆነ የትኛውም ዓይነት ጣልቃ ገብነት እንዲታቀብ እና ጣልቃ ያለመግባትን ዓለም አቀፍ ህግ እንዲያከብር” ጠይቀዋል፡፡