በትግራይ የተፈጠረው ውጥረት በሰላም እንዲፈታ ኢሰመኮ አሳሰበ
ኢሰመኮ እግዱን ተከትሎ በተነሳው ግርግር በክልሉ ሰዎች መቀለሳቸውን፣ መታሰራቸውና በመቀሌና በአዲግራት የአስተዳደሪዎች ቅየራ መደረጉን ጠቅሷል

አቶ ጌታቸው በአስተዳደራቸው ላይ መፈንቅለ መንግስት እየተካሄደ እንደሆነና የፌደራል መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል
በትግራይ የተፈጠረው ለሰላም ስምምነቱና ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ስጋት የሆነው ውጥረት በሰላም እንዲፈታ ኢሰመኮ አሳሰበ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል በሁለት የህወሓት ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ውጥረት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት "በተሟላ መልኩ እንዳይፈጸም" የሚያደርግና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ስጋት የሚፈጥር በመሆኑ በሰላም እንዲፈታ አሳስቧል።
በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል ሲካሄድ የነበረው ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ጥቅምት 2015 ዓ.ም በተፈረመ የሰላም ስምምነት መቋጨቱን ተከትሎ በክልሉ የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር በሚመራው ህወሓት አባላት መካከል በዋናነት የፓርቲው ጉባኤ መካሄድ አለበትና የለበትም በሚል ጉዳይ በሁለት ጎራ ተከፋፍለዋል።
በህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው ቡደን ባለፈው አመት ነሐሴ ወር ምርጫ ቦርድና የኢትዮጵያ መንግስት እውቅና የነፈገውን "የመዳን ጉባኤ" ያካሄደ ሲሆን የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር በነበረውና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት በሆነው አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ጉባኤን በመቃውም ሳይተሳፍ ቀርቷል።
ሁለቱ ቡድኖች ከእዚያን ጊዜ ጀምሮ እርስበርሳቸው በመግለጫ መወጋገዛቸው የተለመደ ቢሆን አቶ ጌታቸው መጋቢት 1፣2017ዓ.ም በሶስት የትግራይ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ላይ እግድ ከጣሉ በኋላ ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ኢሰመኮ በመግለጫው አቶ ጌታቸው እግድ ከጣሉ በኋላ "የህወሓት ተወካይ መሆናቸውን የሚገልጹት አካላት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የጊዜያዊ አስተዳደሩን የመንግሥት ተቋማት ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ተከትሎ ከክልሉ ነዋሪዎች ዕለታዊ እንቅስቃሴ ባሻገር በሰዎች ሰብአዊ መብቶች ላይ አደጋ እና ሥጋት ፈጥረዋል"ብሏል።
ኢሰመኮ እግዱን ተከትሎ በተነሳው ግርግር በክልሉ ሰዎች መቁሰላቸውን፣ መታሰራቸውና በመቀሌና በአዲግራት የአስተዳደሪዎች ቅየራ መደረጉን ጠቅሷል።
አቶ ጌታቸው ከቀናት በፊት በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ስልጣን መጨበጥ የፈለገ አድን ቡድን ክልሉን ወደ ትርምስ እያስገባው ነው ሲሉ በዶክተር ደብረጾዮን የሚመራውን የህወሓት ቡድን መክሰሳቸው ይታወሳል።
አቶ ጌታቸው በዚሁ መግለጫቸው ጥቂት ትግራይ የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች ከኤርትራ መንግስት ጋር ግንኘነት አላቸው፤ የኤርትራም መንግስትም በክልሉ ከተፈጠረው ክፍፍልና ውጥረት ማትረፉ ይፈልጋል ሲሉ ከሰዋል።
በአስተዳደራቸው ላይ መፈንቅለ መንግስት እየተካሄደ እንደሆነና የፌደራል መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው የጠየቁት አቶ ጌታቸው ከዚህ በፊት የነበሩ ሁኔታዎችን በመጥቀስ የፌደራል መንግስት ከሌላኛው ቡድን ጋር ድርድር እንዳያደርግ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ የክልሉን ሁኔታ በተመለከተ በአዲስ አበባ ለሚገኙ ዲፕሎማቶች ማብራሪያ በሰጡት ወቅት በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራውን ቡድን የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዳይፈጸም በማደናቀፍ ከሰዋል።
በደብረጽዮን የሚመራው ህወሓት ግን መንግስት ሳያውቀው ከኤርትራ መንግስት ጋር የተደረገ ግንኙነት የለም ሲል አስተብሏል።
የኤርትራ መንግስት ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል የአቶ ጌታቸው የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ በኤክስ ገጻቸው ኤርትራ በትግራይ የተፈጠረውን ውጥረት የማባባስም ሆነ "የውስጥ ጉዳይ" የሆነውን የፕሪቶሪያውን ስምምነት እንዳይፈጸም የማደናቀፍ ፍላጎት የላትም ብለዋል።
የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመና ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ወደብ ለማግኘት መደራደር እንደምትፈልግ ይፋ ካደረገች በኋላ እንደሻከረ ይነገራል።