በጭና የብዙ ሰዎች የአስከሬን መገኘቱ እንዳሳሰበው ኢሰመኮ አስታወቀ
ትክክለኛውን የሟቾች ቁጥር ለማወቅና ማንነታቸውን ለመለየት ምርመራዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸውንም ነው ያስታወቀው
ኢሰመኮ ወደ አካባቢው የአጥኚዎች ቡድንን እንደሚያሰማራ ገልጿል
በሰሜን ጎንደር ዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ ትናንት ማክሰኞ ጷጉሜ 2 ቀን 2013 ዓ/ም የብዙ ሰዎች የአስከሬን መገኘቱ እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡
ትክክለኛውን የሟቾች ቁጥር ለማወቅና ማንነታቸውን ለመለየት ምርመራዎች በመካሄድ ላይ ናቸው ያለው ኢሰመኮ ሟቾቹ ንጹሃን መሆናቸውን ከሞት የተረፉ ሰዎች እንደሚናገሩ ገልጿል፡፡
ራሱን የትግራይ መከላከያ (TDF) ብሎ የሚጠራው የህወሓት ተዋጊ ኃይል አካባቢውን በተቆጣጠረበት ወቅት ‘ምግብ ካቀረባችሁልን አንጎዳችሁም’ በሚል በገባላቸው ቃል ተማምነው ያልሸሹ ንጹሃን ዜጎች እንደነበሩ ለማወቅ ስለመቻሉም ነው ኢሰመኮ ያስታወቀው፡፡
ባሳለፍነው ሃሙስ እና አርብ (ነሐሴ 28 እና 29 ቀን 2013) የመከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው እየተቃረበ መምጣቱን ተከትሎ ተዋጊዎቹ ንጹሃኑንን ገድለው መሸሻቸውንም የአካባቢውን ነዋሪዎች እና ባለስልጣናት ንግግር ዋቢ አድርጎ ጠቁሟል፡፡
በክልሉ የሚያካሂደው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምርመራ አካል የሆኑ የምርመራ ባለሙያዎቹን ወደ ዳባት እና አካባቢው እንደሚያሰማራም አስታውቋል፡፡
የሲቪል ዜጎች እና መሰረተ ልማቶች ደህንነት እንዲጠበቅም ኢሰመኮ በድጋሚ የማሳሰቢያ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአካባቢው የነበሩ የህወሓት ተዋጊዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ200 በላይ ንጹሃን ተገድለዋል ሲሉ የመንግስት ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡