ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ምን ምላሽ ሰጠች?
አሜሪካ በመንግስት ሃይሎች እና በታጣቂዎች ተፈጸሙ ስላለቻቸው የጦር ወንጀሎች ያወጣችው መግለጫ “አዲስነት የሌለውና ወቅቱን ያልጠበቀ ነው” በሚል ነው ኢትዮጵያ የተቃወመችው
መግለጫው የሰላም ስምምነቱንና የሽግግር ፍትህ የማረጋገጥ ሂደቱንም ግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑንም አስታውቋል
አሜሪካ በሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት የመንግስት ወታደሮችን እና የህወሃት ታጣቂዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ መግለጫ አውጥታለች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ያወጣው መግለጫ፥ በህዳር ወር 2022 ከተደረሰው የሰላም ስምምነት በኋላ ግጭቱ ቆሞ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችም በከፍተኛ ደረጃ መቀነሳቸውን ያነሳል።
የኤርትራ ወታደሮች መውጣት እና የኢትዮጵያ መንግስት የሽግግር ፍትህን ለማስፈን የጀመራቸውን ተግባራት በበጎ ጎኑ ያነሳው መግለጫው፥ ይሁን እንጂ በሰሜን ኢትዮጵያ በንጹሃን ላይ የተፈጸመው ወንጀል ሳይጠቀስ ሊታለፍ አይገባም ብሏል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንም፥ “የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች፣ የኤርትራ ወታደሮች፣ የአማራ ሃይሎች እና የህወሃት ታጣቂዎች”ን ለተፈጸሙት ወንጀሎች ተጠያቂ ያደረጉበትን መረጃ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
መግለጫው ከህወሃት ውጭ ያሉትን (የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደሮች እንዲሁም የአማራ ሃይሎች) በግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እና መሰል በሰብአዊነት ላይ የተቃጣ ወንጀል ፈጽመዋል ሲል ይከሳል።
- ህወሓት አቶ ጌታቸው ረዳን ለጊዜያዊ መንግስት ፕሬዝዳንትነት እጩ አድረጎ መረጠ
- በሰሜኑ ጦርነት አጥፊዎች የሚጠየቁበት እና ተጎጂዎች የሚካሱበት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ተዘጋጀ
የአማራ ሃይሎች በምዕራብ ትግራይ የዘር ፍጅት ፈጽመዋል የሚል ክስን የሚያስከትለው መግለጫው፥ የትግራይ ሃይሎች (ህወሃት) በምን አይነት የወንጀል ድርጊት እንደተሳተፉ አልጠቀሰም።
የተፈጸሙትን ወንጀሎች ማንሳትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እንደሚያግዝ የጠቆመው የአሜሪካ መግለጫ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ውድቅ ተደርጓል።
የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፥ የአሜሪካ መግለጫ “አዲስነት የሌለውና ጊዜውን ያልጠበቀ” ነው በሚል ተቃውሞታል።
“ኢትዮጵያ የተሽፋፈነ ውግዘትን አትቀበልም” ያለው መግለጫው፥ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርትን ተመርኩዞ የወጣው አዲስ መግለጫ ምንም አዲስ ነገር እንደሌለውም ጠቁሟል።
የአሜሪካ መግለጫ ያስቀመጠው ወቀሳ ሚዛን የሳተና (የህወሃት ሃይሎችን) የወንጀል ተጠያቂነት “መርጦ” ለመቀነስ ጥረት ያደረገ ስለመሆኑም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ያመላከተው።
ትናንት የወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ላይ ምክክር እያደረገችና ተጠያቂነትን ለማስፈን ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረግ በጀመረችበት ወቅት የወጣ በመሆኑም “ወቅቱን ያልጠበቀና ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የሚያውክ” ነው በሚል ተቃውሞታል።
መግለጫው አንድ ማህበረሰብ በሌላው ላይ እንዲነሳ ሊገፋፋ የሚችል መሆኑን በመጥቀስም ፥ “ክስና ወቀሳን የመደልደል ሙከራው” የሰላም ስምምነቱን ሊያውከው እንደሚችል አብራርቷል።
ያም ሆኖ ግን አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝትና በግልጽነት በተካሄደው ምክክር የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እየተሻሻለ እንደሚሄድ ኢትዮጵያ ታምናለች ነው ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫን የተቃወመችው ኢትዮጵያ የትኛውም ወንጀል ፈጻሚ ተጠያቂ የሚሆንበትን አሰራር ለመዘርጋት ዝግጅቷን መቀጠሏንም አስታውቃለች።