ኤጀንሲዎቹ በሉዓላዊ ሃገራት ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት ባለፈ እንደ ‘ምስለኔ’ ለመሆን ይቃጣቸዋልም ነው ሚኒስትሩ ያሉት
የኤርትራ የመረጃ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጄንሲዎች ኃላፊነታቸውን ወደ ጎን በመተው በቀጣናው (ምስራቅ አፍሪካ) ሉዓላዊ ሃገራት ጣልቃ የመግባት መጥፎ ልማድ አዳብረዋል ሲሉ ወቀሱ፡፡
ይህን ለባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ታዝበናል ያሉት ሚኒስትሩ መጥፎ ያሉትን ይህን ልማድ “የማይታረቅ” ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ኤጀንሲዎቹ የሉዓላዊ ሃገራቱ ‘ምስለኔ’ ለመሆን እንደሚቃጣቸውም ነው በትዊተር የማህበራዊ ገጻቸው ያሰፈሩት፡፡
ሚኒስትሩ የቅርብ ጊዜያት ክስተቶች ጭምር ይህንኑ የሚያረጋግጡ ናቸው ያሉም ሲሆን የአብዛኞቹን የድርጅቱን ኤጀንሲዎች መልካም ተግባር የሚያጎድፈው ይህ ስራ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀዋል፡፡
ለቀጣናው ህዝቦች ደህንነት እና ለተቋማቱ መልካም ስም ሲባል ሊታረም እንደሚገባውም ነው ያሳሰቡት፡፡
ሆኖም ሚኒስትሩ ወቀሳውን ምንን ታሳቢ አደርገው እንዳቀረቡት አልገለጹም፡፡
በተያያዘ ሌላ ዜና የድርጅቱ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባሸሌት በትግራይ ንጹሃንን ዒላማ አድርገው የሚፈጸሙ የህግ ጥሰቶችን፣ግድያዎችን እና ዘረፋዎችን የተመለከቱ መረጃዎች ደርሰውናል በሚል ዛሬ ባወጡት መግለጫ ሰብዓዊ ድጋፎች ባልተቆራረጠ መልኩ ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ኮሚሽነሯ በማይካድራ እና በሌሎችም አካባቢዎች የተፈጸሙ ዘግናኝ ሰብዓዊ ጥቃቶች የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን የመጀመሪያ ሪፖርት መነሻ አድርገው በገለልተኛ አካል ይበልጥ ሊጣሩ እና ሊመረመሩ ይገባል ሲሉም ነው ያሳሰቡት፡፡
ኢትዮጵያ ያሉባትን ብሄር ተኮር የልዩነት ችግሮች ተጠያቂነት ባለው አካታች የውይይት እና የእርቅ መንገድ ልትፈታ ይገባልም ብለዋል፡፡
ዛሬ መደበኛ ሳምንታዊ መግለጫን የሰጡት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ግን በገለልተኛ አካል ይጣራ የሚለው ሃሳብ እንደማያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ከህግ ማስከበር ዘመቻው ጋር በተያያዘ አጋጥመዋል የተባሉትን ጉዳቶች በገለልተኛነት ለማጣራት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በቂ እንደሆነም ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት፡፡